ኢትዮጵያ እና አሜሪካ ያላቸውን የቆየ ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር ያለመ የሁለትዮሽ ምክክር በዋሽንግተን ዲሲ አካሂደዋል።
በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዴዮን ጢሞቴዎስ የተመራውና የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማክሮ ኢኮኖሚ አማካሪ አምባሳደር ግርማ ብሩ እንዲሁም የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አምባሳደር ሬድዋን ሁሴንን ያካተተው የኢትዮጵያ ልዑክ፣ ከአሜሪካ አቻዎቻቸው ጋር በጋራ ጉዳዮች ላይ ሰፊ ውይይት አድርገዋል።
በሁለቱ ሀገራት መካከል የተደረገው ይህ ውይይት በሦስት ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ ትኩረቱን ያደረገ ነበር።
እነሱም የኢኮኖሚ ብልጽግና፣ ንግድ እና ኢንቨስትመንት፤ የመከላከያ እና የደህንነት ትብብር እንዲሁም ቀጠናዊ ሰላምና መረጋጋትን ማሳደግ የሚሉ መሆናቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል።
ይህ የተመሠረተው የሁለትዮሽ የምክክር ማዕቀፍ በኢትዮጵያ እና በአሜሪካ መካከል ያለውን የረጅም ጊዜ ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር እና ዘላቂ ለማድረግ ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው ይጠበቃል።