Search

"የፍትህ፣ የመሬትና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ኮሚሽነር ዘገየ አስፋው፦ ከሕግ ምሁርነት እስከ ሀገራዊ ምክክር

ማክሰኞ ግንቦት 04, 2018 464

በኢትዮጵያ ዘመናዊ የታሪክ ጉዞ ውስጥ ጉልህ አሻራ ያሳረፉት ኮሚሽነር ዘገየ አስፋው፣ በሕይወት ዘመናቸው ለሀገራቸውና ለወገኖቻቸው በታማኝነትና በቅንነት ሲያገለግሉ ቆይተው በተወለዱ በ84 ዓመታቸው ትላንት ግንቦት 3 ቀን 2018 ዓ.ም ምሽት ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል።

ኮሚሽነር ዘገየ አስፋው በ1934 ዓ.ም በምዕራብ ሸዋ ተወልደው ያደጉ ሲሆን፣ በትምህርት ሕይወታቸውም የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በቀድሞው ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ፣ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ደግሞ በአሜሪካ በሚገኘው ዊስኮንሲን ማዲሰን ዩኒቨርሲቲ በሕግ ሙያ አግኝተዋል።

የኮሚሽነር ዘገየ የሥራ ዘመን በከፍተኛ የመንግሥት የኃላፊነት እርከኖች የተሞላ ነበር። በተለይም በቀድሞዎቹ የመሬት አስተዳደር፣ የግብርና እና የሰፈራ፣ የፍትሕ እንዲሁም የሥራ እና ማህበራዊ ጉዳዮች ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች በሚኒስትርነት በማገልገል ሀገራዊ ግዴታቸውን ተወጥተዋል።

ስማቸው በብዙዎች ዘንድ በክብር እንዲነሳ ካደረጉት ታሪካዊ ተግባራት መካከል በ1967 ዓ.ም የወጣውን ዝነኛውን የ"መሬት ላራሹ" አዋጅ በማርቀቅና በተግባር እንዲተረጎም በማስፈጸም ረገድ የተጫወቱት ግንባር ቀደም ሚና ተጠቃሽ ነው።

ከመንግሥት የሥራ ኃላፊነት ባሻገር፣ ኮሚሽነር ዘገየ በሰብዓዊ ተግባራትና በሲቪል ማህበረሰብ ግንባታ ውስጥ የነበራቸው ሚና እጅግ ሰፊ ነበር። "ሁንዴ" የተባለ ግብረ-ሰናይ ድርጅት እና "ቡሳ ጎፋ" የተባለ የማይክሮ ፋይናንስ ተቋምን በማቋቋም የብዙዎችን ሕይወት መለወጥ የቻሉ ጠንካራ ባለሙያ ነበሩ።

በተለይም በገጠሩ የሀገራችን ክፍል በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን በማውገዝ እና መፍትሔ በማመንጨት ረገድ እንደ አንድ ቀዳሚ የሰብዓዊ መብት አንቂ ይታወቃሉ። ከአርሶ አደሮችና ከአርብቶ አደሮች ጋር በመሆን በአካባቢ ጥበቃና በኑሮ ማሻሻል ዙሪያ የሠሩት ሥራ በአርአያነት የሚጠቀስ ነው።

ባለፉት አራት ዓመታትም ከየካቲት 2014 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ሕይወታቸው ማለፊያ ድረስ በኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ውስጥ በኮሚሽነርነት ሲያገለግሉ ቆይተዋል። በኮሚሽኑ ቆይታቸውም በትጋት፣ በታማኝነትና በሀገር ፍቅር ስሜት ሥራቸውን ሲያከናውኑ የቆዩ ሲሆን፣ ለሥራ ባልደረቦቻቸውም የአርአያነት ምንጭ ነበሩ።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በኮሚሽነሩ ሕልፈት የተሰማውን ጥልቅ ሐዘን በመግለጽ፣ ለቤተሰቦቻቸውና ለወዳጅ ዘመዶቻቸው መጽናናትን ተመኝቷል።