በኬንያ መዲና ናይሮቢ የተካሄደውና "አፍሪካ ፎርዋርድ" (Africa Forward) የሚል ስያሜ የተሰጠው ታሪካዊ ጉባኤ፣ በፈረንሳይ እና በአፍሪካ ሀገራት መካከል ባለው ግንኙነት ላይ አዲስና ተስፋ ሰጪ ምዕራፍ ከፍቷል።
የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን እና የኬንያው ፕሬዝዳንት ዊልያም ሩቶ በጋራ የመሩት ይህ መድረክ፣ ፓሪስ ከቀድሞው የ"ፍራንሳፍሪክ" የፖለቲካና የኢኮኖሚ ጥገኝነት ትውፊት በመውጣት፣ ወደ ሚዛናዊና ዘመናዊ ስትራቴጂካዊ አጋርነት መሸጋገሯን ያበሰረበት ክስተት ሆኗል። በተለይም ፈረንሳይ ከቀድሞ ቅኝ ግዛቶቿ ባለፈ ወደ ምስራቅ አፍሪካና ወደ እንግሊዝኛ ተናጋሪ ሀገራት ፊቷን ማዞሯ የግንኙነቱን አድማስ ያሰፋ ታላቅ እርምጃ ተደርጎ ተወስዷል።
ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በናይሮቢ ዩኒቨርሲቲ ባደረጉት ንግግር፣ አፍሪካን እንደ ፈረንሳይ የግል ይዞታ የማየት አሮጌ ዝንባሌ ማብቃት እንዳለበት በግልጽ አንጸባርቀዋል። አፍሪካ ራሷን ለመቻል ኢንቨስትመንትና እኩል አጋርነት እንጂ የአውሮፓ መሪዎች መመሪያ እንዲሰጧት እንደማትፈልግ የገለጹት ፕሬዝዳንቱ፣ የጠባቂነት ዘመን አብቅቶ የትብብር ዘመን መጀመሩን አረጋግጠዋል።
ይህ አዲስ አቅጣጫ ፈረንሳይ በአፍሪካ ያላትን ሚና ከወታደራዊ ጡንቻ ወደ "ለስላሳ ኃይል" ማለትም ወደ ኢንቨስትመንት፣ ባህልና ቴክኖሎጂ ለመቀየር ያላትን ጽኑ ፍላጎት የሚያሳይ ነው።
የናይሮቢው ጉባኤ በንግግር ብቻ የተወሰነ ሳይሆን፣ በአጠቃላይ 27 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት ግዙፍ የኢኮኖሚ ስምምነት የተፈረመበት ስኬታማ መድረክ ነበር። ይህ ኢንቨስትመንት በዋናነት በታዳሽ ኃይል፣ በዲጂታል ቴክኖሎጂ፣ በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ፣ በባህር ኢኮኖሚ እና በዘመናዊ ግብርና ላይ ያተኮረ ሲሆን፣ በአፍሪካና በፈረንሳይ ውስጥ እስከ 250,000 የሚደርሱ አዳዲስ የሥራ ዕድሎችን እንደሚፈጥር ይጠበቃል።
በተጨማሪም ፈረንሳይና ኬንያ በመረጃ ልውውጥና በባህር ላይ ደኅንነት ዙሪያ የአምስት ዓመት የመከላከያ ስምምነት መፈረማቸው፣ ግንኙነቱ ዘርፈ ብዙና የሁለቱንም ሀገራት ጥቅምና ደኅንነት የሚያስከብር መሆኑን አረጋግጧል።
ኬንያ ይህንን ጉባኤ በማስተናገድ ረገድ የነበራት ሚና በአህጉሪቱ ዲፕሎማሲ ውስጥ "ድልድይ ሰሪነትን" ያረጋገጠ ነው። የኬንያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሙሳሊያ ሙዳቫዲ እንደገለጹት፣ ጉባኤው በአፍሪካ ሀገራት መካከል ያለውን ሰው ሰራሽ የቋንቋ አጥር በማፍረስ የጋራ ብልጽግናን ለማምጣት ይረዳል።
ይህም አፍሪካ ከኃያላን ሀገራት ጋር የምታደርገውን ግንኙነት በራሷ ፍላጎትና በስትራቴጂካዊ ጥቅሟ ላይ ለመመሥረት ያላትን ዝግጁነት ያሳየ ነው። ምንም እንኳን የቆዩ የታሪክ ጠባሳዎችና ተግዳሮቶች ባይጠፉም፣ የናይሮቢው ጉባኤ ግን ፈረንሳይና አፍሪካ እጅ ለእጅ ተያይዘው ወደፊት ለመራመድ የቆረጡበት የዲፕሎማሲ ድል ሆኖ በታሪክ መዝገብ ላይ ይሰፍራል።
በሰለሞን ገዳ