130 ሚሊዮን የሚጠጋ ሕዝብን የምታስተዳድረው ኢትዮጵያ፣ በዓለም ታሪክ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሕዝብ ይዛ የባሕር በር አልባ (Landlocked) ሆና እንድትቀጥል የተፈረደባት ብቸኛ አገር ሆናለች። ይህ "የጂኦግራፊ እስራት" ተብሎ የሚጠራው ተፈጥሯዊና ሰው ሠራሽ ማነቆ፣ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ከመገደብ ባለፈ ብሔራዊ ሉዓላዊነቷን የፖለቲካ ፈቃድ አሳልፎ ሰጥቷል።
ጥናቶች እንደሚያሳዩት የባሕር በር አልባ መሆን የአንድን አገር አጠቃላይ የልማት ደረጃ 20% ገደማ ዝቅ ያደርገዋል። ይህ "የባሕር በር አልባነት ቅጣት" በኢኮኖሚ አመልካቾች ላይ በግልጽ ይንጸባረቃል። የባሕር በር የሌላቸው አገራት አማካይ የሕይወት ዘመን 55.9 ዓመት ሲሆን፣ የባሕር በር ያላቸው አገራት ግን 63.6 ዓመት ይደርሳሉ። በተመሳሳይ የክትመት መጠን በባሕር በር አልባ አገራት 28.2% ብቻ ሆኖ ሳለ፣ የባሕር በር ባላቸው አገራት ግን 49.0% መድረሱ የንግድ ትስስር ያለውን ሚና ያሳያል።
የኢትዮጵያ ፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት (PSI) ይፋ ባደረገው መረጃ መሠረት፣ የወደብ አልባ መሆንና ተያያዥ ችግሮች በኢትዮጵያ ላይ በየዓመቱ ከ19 ቢሊዮን እስከ 31 ቢሊዮን ዶላር የሚደርስ የአጠቃላይ የአገር ውስጥ ምርት (GDP) ኪሳራ ያስከትላሉ። ኢትዮጵያ በየዓመቱ ወደ 2 ቢሊዮን ዶላር ገደማ ለወደብ አገልግሎት ክፍያ የምታወጣ ሲሆን፣ ይህም ከኢትዮጵያ የጠቅላላ የውጭ ዕዳ ክፍያ 193% ጋር እኩል መሆኑ አስደንጋጭ ሃቅ ነው።
የሎጂስቲክስ ማነቆ እና የሉዓላዊነት ጥገኝነት
በኢትዮጵያ የሎጂስቲክስ ወጪ የአንድን ምርት ዋጋ ከ20% እስከ 30% የሚሸፍን ሲሆን፣ ይህ ቁጥር በዓለም አቀፍ ደረጃ ከ8% እስከ 12% ብቻ ነው። አንድ ኮንቴይነር ምርት ከባሕር በር አልባ አገር ወደ ውጭ ለመላክ እስከ 3,400 ዶላር የሚጠይቅ ሲሆን፣ የባሕር በር ባላቸው አገራት ግን ይህ ወጪ 1,300 ዶላር ብቻ ነው። ይህ የዋጋ ልዩነት የኢትዮጵያን ምርቶች በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ እንዳይሆኑ አድርጓቸዋል።
ከኢኮኖሚው ባሻገር፣ የባሕር በር አልባነት የብሔራዊ ደኅንነት ስጋት ነው። የኢትዮጵያ ንግድ 95% በላይ በጅቡቲ ወደብ ላይ ጥገኛ መሆኑ፣ የኢትዮጵያን የንግድ ደኅንነት በጎረቤት አገር ፖለቲካዊ መረጋጋትና አስተዳደራዊ ውሳኔዎች ላይ እንዲንጠለጠል አድርጎታል። በዓለም አቀፍ የባሕር ሕግ (UNCLOS) አንቀጽ 124 እስከ 132 የባሕር በር አልባ አገራት የመሸጋገሪያ ነፃነት እንዳላቸው ቢደነግግም፣ አፈጻጸሙ ግን በመሸጋገሪያ አገራት "ፈቃድ" ላይ የወደቀ በመሆኑ ኢትዮጵያን ለዓመታት ለዲፕሎማሲያዊ ጫና ዳርጓታል።
"የቀይ ባሕር ትውልድ" መነሳት
የዛሬዋ ኢትዮጵያ 65 በመቶ የሚሆነው ሕዝቧ ወጣት ነው። ይህ "የቀይ ባሕር ትውልድ" (Gen-Z እና Gen-Alpha) የባሕር በር አልባነትን እንደ ቋሚ ዕጣ ፈንታ ሳይሆን እንደ "ታሪካዊ ስህተት" ይመለከተዋል። ወጣቱ ትውልድ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን እና የባሕር በር ጥያቄን እንደ "ሁለቱ ውኃዎች" ዶክትሪን በማስተሳሰር ለብሔራዊ ብልጽግና ዋስትና አድርጎታል።
ይህ ትውልድ ማኅበራዊ ሚዲያዎችን በመጠቀም የባሕር በር ጥያቄው ሕጋዊ፣ ታሪካዊና ኢኮኖሚያዊ ፍትሃዊነትን የተላበሰ መሆኑን ለዓለም እያስተጋባ ነው። በፖለቲካ ሴራ የተከሰተው የባሕር በር ማጣት በ130 ሚሊዮን ሕዝብ ላይ የተፈረደ "የጂኦግራፊ እስር" መሆኑን በመረዳት፣ ይህንን እስራት መበጠስን የትውልድ ተልዕኮ አድርጎታል።
ባለፉት 20 ዓመታት ውስጥ ብቻ በወደብ ችግር ምክንያት ኢትዮጵያ ማግኘት ከነበረባት 38 ቢሊዮን ዶላር በላይ አጥታለች። ይህ የገንዘብ ወጪና የኢኮኖሚ ማነቆ ለአንዲት ታዳጊ አገር የማይሸከሙት ከባድ ቀንበር ነው። ይሁን እንጂ አሁን እየተወሰዱ ያሉት ስልታዊ እርምጃዎችና የአዲሱ ትውልድ ቁርጠኝነት ኢትዮጵያ ከዚህ "የጂኦግራፊ እስራት" የምትወጣበት ጊዜ ሩቅ እንዳልሆነ ያመለክታሉ።ኢትዮጵያ የባሕር በር የማግኘትዋ ጉዳይ ቅንጣት የሚያጠራጥር አይደለም፡፡ ጥያቄው የቅንጦት ጉዳይ ሳይሆን የህልውና፣ የፍትህ እና የሉዓላዊነት ጥያቄ ነውና።
በአዶኒያስ ወ/አረጋይ