አፍሪካ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ውስጥ የሚገባትንና ፍትሐዊ የሆነ ድምፅ ሊኖራት እንደሚገባ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አስገነዘቡ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን ያሉት ኢትዮጵያ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን የ80 ዓመታት ጉዞ ምክንያት በማድረግ ትላንት ባዘጋጀችው ልዩ የመታሰቢያ ቴምብሮች ማስተዋወቂያ መርሐ ግብር ላይ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በንግግራቸው፤ ድርጅቱ የዛሬውን ዓለም እውነታዎች በሚያንፀባርቅ፣ ይበልጥ ፍትሐዊ እና ሁሉንም እኩል በሚወክል መልኩ ሊሻሻል እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተው አሳስበዋል።
በተለይም አህጉሪቱ በወደፊት ዕጣ ፈንታዋ ላይ በቀጥታ በሚወስኑ ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ ጠንካራ ድምፅ ሊኖራት እንደሚገባ በመጥቀስ፤ አፍሪካ ለተሻለ ዓለም አቀፋዊ ሥርዓት ግንባታ የድርሻዋን ለመወጣትና ትልቅ ኃላፊነት ለመውሰድ ዝግጁ መሆኗን ዳግም አረጋግጠዋል።
በተጨማሪም ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በሰላምና ደኅንነት፣ በልማት፣ በአየር ንብረት ለውጥና በቴክኖሎጂ ዕድገት ዙሪያ በቁርጠኝነት ሊሠራ እንደሚገባ ጥሪ አቅርበዋል።
ወቅታዊ ተግዳሮቶች እርስ በእርሳቸው የተሳሰሩ በመሆናቸው ጠንካራ አጋርነትና ዓለም አቀፍ ትብብርን እንደሚጠይቁ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠቁመዋል።
ከፊታችን ያለው ተግባር ግልጽ በመሆኑ ዓለም አቀፋዊ ሥርዓቱን ከዘመኑ ጥያቄዎች ጋር በሚጣጣም መልኩ ማደስና ማላመድ የግድ ይላል ሲሉም ገልጸዋል።
በመሀመድ ፊጣሞ