Search

ከንቲባ አዳነች አቤቤ በበጎነት መንደር የተገነባውን 29ኛውን የተስፋ ብርሃን የምገባ ማዕከል መርቀው ሥራ አስጀመሩ

ሓሙስ ግንቦት 06, 2018 60

የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በልደታ ክፍለ ከተማ የተገነባውንና ለከተማዋ 29ኛ የሆነውን "የተስፋ ብርሃን" የምገባ ማዕከል መርቀው ሥራ አስጀመሩ።
ማዕከሉ ማኅበራዊ ፍትህን ለማንገሥ የሚከናወኑ የበጎነት ተግባራት አካል ሲሆን፣ በተለይም በልማት ምክንያት ተነስተው በተገነቡ 492 ቤቶች ውስጥ ለሚኖሩ 2 ሺህ 460 ነዋሪዎች ትልቅ እፎይታ እንደሚሆን ከንቲባዋ ገልጸዋል።
በተለይ አረጋውያን፣ ለማኅበራዊ ችግር የተጋለጡና ድጋፍ የሚሹ ወገኖች በሚኖሩበት በዚህ "የበጎነት መንደር" ውስጥ የተከፈተው ማዕከል፤ ነዋሪዎች ንጹሕና ትኩስ ምግብ በቀን አንድ ጊዜ እንዲያገኙ ያስችላል።
ከንቲባዋ በመልዕክታቸውም "በከተማችን ለችግር የተጋለጡ ወገኖች ምግብ ፍለጋ ወደ ጎዳና የሚወጡበት ምክንያት የለም፤ በሁሉም ክፍለ ከተማ ባሉ 29 የምገባ ማዕከላት በመገኘት መመገብ ይቻላል" ብለዋል።
ከምገባ ማዕከሉ በተጨማሪ በመንደሩ ውስጥ የሥራ ዕድል የተፈጠረባቸው የእንጀራ መጋገሪያ፣ የልብስ ስፌት፣ የፀጉር ሥራ እና የልጆች መጫወቻ ስፍራዎች ተደራጅተው ለነዋሪዎቹ አገልግሎት መስጠት መጀመራቸው ተገልጿል።
ከንቲባ አዳነች አቤቤ ለማዕከሉ ግንባታና ለምገባ ሂደቱ ድጋፍ ላደረገው ዳሽን ባንክም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።