የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ5ኛ ዓመት የስራ ዘመኑ 21ኛ መደበኛ ስብሰባው የሕብረት ሥራ ማህበራትን አሠራር ዘመናዊ የሚያደርግ ረቂቅ አዋጅን መርምሮ አፅድቋል።
በምክር ቤቱ የግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ሰለሞን ላሌ የሪፖርትና የውሳኔ ሐሳብ ያቀረቡ ሲሆን፣ ረቂቅ አዋጁ በርካታ ባለድርሻ አካላት የተሳተፉበትና ነባራዊ ችግሮችን የሚፈታ መሆኑን በዝርዝር አስረድተዋል።
እንደ ሰብሳቢው ገለጻ፣ አዋጁ በተበታተነ ሁኔታ በተለያየ እርከን ተደራጅተው የሚገኙና ውጤታማ ያልሆኑ ማህበራት ሰብሰብ ብለው እንዲደራጁ በማድረግ፣ የአሠራር ድግግሞሽን በማስቀረት ትርፋማነታቸውንና የአባላቱን ተጠቃሚነት ከፍ የሚያደርግ ሥርዓት የሚዘረጋ ነው።
ማህበራቱ በሰለጠነ የሰው ኃይልና በቴክኖሎጂ የታገዘ የቢዝነስ አሠራርን እንዲከተሉ የሚያግዘው ይህ አዋጅ፤ በአመራር ብቃት፣ በፋይናንስ አያያዝና በተጠያቂነት ረገድ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን ለመቅረፍ ታሳቢ ተደርጎ የተዘጋጀ ነው።
በተለይም የፋይናንስ አቅርቦት ችግርን ለመፍታት ማህበራት እስከ 40 በመቶ የሚሆነውን ድርሻቸውን ለኢንቨስተሮች መሸጥ የሚያስችላቸው ነው።
ይህም ማህበራቱ መሬትና መጋዘን ሲያቀርቡ፣ ባለሀብቱ ደግሞ ካፒታልና ቴክኖሎጂን ይዞ በመቅረብ ምርታማነትን እንዲያሳድጉ ዕድል ይሰጣል።
በተጨማሪም ሴቶች፣ ወጣቶች እና አካል ጉዳተኞች ለብቻቸው እንዲደራጁ ከመፍቀዱም በላይ፣ በሌሎች ማህበራት ውስጥ በሚሳተፉበት ወቅት ሴቶች 50 በመቶ፣ ወጣቶች 10 በመቶ፣ እንዲሁም አካል ጉዳተኞች 10 በመቶ የአመራርነት ድርሻ እንዲኖራቸው መደንገጉ የአካታችነት ችግርን የሚቀርፍ መሆኑ ተመላክቷል።
በሳራ ሳህለሥላሴ