የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ፣ ድርጅቱ የተመሰረተበትን 80ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ በኢትዮጵያ የተዘጋጀውን ልዩ የቴምብር ስብስብ ከፍተዋል።
ዋና ጸሐፊው በሥነ-ሥርዓቱ ላይ ባደረጉት ንግግር፣ አዲሱ የመታሰቢያ ቴምብር የተመድን 80ኛ ዓመት ከማክበር ባለፈ በኢትዮጵያና በተመድ መካከል ያለውን ታሪካዊና የጠበቀ አጋርነት የሚያሳይ መሆኑን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በአውሮፓውያኑ 1945 የተመድ ቻርተርን ከፈረሙ የመጀመሪያዎቹ 51 አገራት አንዷ መሆኗን ያነሱት ዋና ጸሐፊው፣ አብዛኛው የአፍሪካ አህጉር በቅኝ ግዛት ስር በነበረበት ወቅት ነጻነቷን ጠብቃ የቆየች ጥንታዊ የስልጣኔ ማሳያ መሆኗን አውስተዋል።
ኢትዮጵያ ሌሎች የአፍሪካ አገራት ነጻነታቸውን እንዲያገኙና የድርጅቱ አባል እንዲሆኑ ላበረከተችው ግንባር ቀደም ሚናም አድናቆታቸውን ገልጸዋል።
አዲስ አበባ "በብርሃን ፍጥነት" እየተለወጠች ያለች ከተማ መሆኗን የጠቀሱት ዋና ጸሐፊው፣ ከተማዋ የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ እና በዓለም ላይ ካሉ ትላልቅ የተመድ የሥራ ጣቢያዎች አንዷ በመሆን ያላትን ስፍራ አጉልተዋል።
ኢትዮጵያውያን ወታደራዊ እና ሲቪል ሰራተኞች በዓለም ዙሪያ በሰላም ማስከበር ሥራዎች ላይ እያበረከቱት ላለው ታላቅ አስተዋጽኦም እውቅና ሰጥተዋል።
ዋና ጸሐፊው አያይዘውም የዓለም አቀፍ ተቋማት አፍሪካ በቅኝ አገዛዝ ስር በነበረችበት ወቅት የተፈጠሩ በመሆናቸው፣ ይህንን ታሪካዊ በደል ለመቀልበስ የጸጥታው ምክር ቤት በአስቸኳይ መሻሻል እንዳለበትና ለአፍሪካ ቋሚ ውክልና ቅድሚያ ሊሰጠው እንደሚገባ አሳስበዋል።
ኢትዮጵያ በኢኮኖሚ ልማት የላቀ ዕድገት እያሳየች መሆኗን ጠቅሰው፣ ይህም አፍሪካ በዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ውስጥ የውሳኔ ሰጪነት ሚና ሊኖራት እንደሚገባ ማረጋገጫ መሆኑን አስታውቀዋል።
ዋና ጸሐፊው ሰላም፣ ፍትህ እና ብልጽግናን ለሁሉም የማስፈን የተመድ ዋና ቃል ኪዳን ዛሬም አስፈላጊ መሆኑን ገልጸው፣ ለተሻለች አፍሪካና ዓለም በሚደረገው ጉዞ ላይ ኢትዮጵያ ግንባር ቀደም ሚናዋን እንድትወጣ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።
በንፍታሌም እንግዳወርቅ