Search

ኢትዮጵያ እና ፈረንሳይ፦ ከታሪካዊ ወዳጅነት ወደ ስትራቴጂያዊ አጋርነት

ረቡዕ ግንቦት 05, 2018 310

የኢትዮጵያና የፈረንሳይ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ረጅም ዘመናትን ያስቆጠረና በጽኑ ታሪካዊ መሠረት ላይ የቆመ ነው፡፡
 
የሁለቱ ሀገራት ትብብር ከተለመደው የእርዳታ ሰጭና ተቀባይ ግንኙነት ባሻገር፣ በጋራ ጥቅም እና በእርስ በእርስ መከባበር ላይ የተገነባ መሆኑ ለየት ያደርገዋል፡፡
 
ይህ ወዳጅነት የጊዜን ፈተና አልፎ ዛሬ ላይ ለቀጣናዊ ሰላምና ለኢኮኖሚ ትስስር ፋይዳ ያለው ወሳኝ አጋርነት ሆኗል፡፡

ለዚህ ዘላቂና ውጤታማ ግንኙነት ቀዳሚውና ትልቁ ማሳያ፤ ከመቶ ዓመታት በፊት በሁለቱ ሀገራት ስምምነት ተገንብቶ አዲስ አበባን ከጅቡቲ ያቆራኘው የባቡር መሠረተ ልማት ነው፡፡
 
ይህ ግዙፍ ፕሮጀክት ኢትዮጵያን ከዓለም አቀፍ የንግድ መስመር ጋር በማስተሳሰር ረገድ የታሪክ አሻራውን ያሳረፈ ሲሆን ግንኙነቱ ገና ከጥንቱ በሉዓላዊ እኩልነትና በአጋርነት ላይ የተመሰረተ መሆኑን በተግባር ያሳየ ነበር፡፡

የባቡር መስመሩ የሁለቱን ሀገራት የንግድ ልውውጥ ከማሳለጡ ባለፈ፣ የፈረንሳይን ቴክኖሎጂ ከኢትዮጵያ ልማት ጋር ያቆራኘ ቀዳሚ ስኬት ተደርጎ ይወሰዳል፡፡

በአሁኑ ወቅት የሁለቱ ሀገራት ስትራቴጂካዊ ግንኙነት ዘመኑን ወደዋጁና ቀጣናዊ ፋይዳ ወዳላቸው ዘርፎች ይበልጥ እየተሸጋገረ ይገኛል፡፡
 
በተለይም ፈረንሳይ፤ ኢትዮጵያ የባሕር በር የማግኘትና የመጠቀም ጥያቄዋ ፍጹም ተገቢና ሕጋዊ መሆኑን በግልጽ የተቀበለች ሀገር ነች፡፡

የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን እና በኢትዮጵያ የፈረንሳይ አምባሳደር አሌክሲስ ላሜክ በተደጋጋሚ እንደገለጹት ኢትዮጵያ የባሕር በር ለማግኘት የምታደርገው ጥረት በዓለም አቀፍ ሕግና በሰላማዊ ውይይት ላይ የተመሰረተ እንዲሆን ፈረንሳይ ሙሉ ዲፕሎማሲያዊ ድጋፏን ትሰጣለች፡፡

የፈረንሳይ ድጋፍ በዲፕሎማሲያዊ ዕውቅና ብቻ የተገደበ አይደለም፡፡ የኢትዮጵያን የባሕር ኃይል መልሶ ለማደራጀትና አባላቱን በከፍተኛ ሙያዊና ቴክኒካዊ ሥልጠናዎች ለማብቃት የተጀመረው የመከላከያ ትብብር፣ ሀገራቱ በቀጣናዊ የባሕር ደኅንነትና ሰላም ላይ ያላቸውን የጋራ ቁርጠኝነት የሚያሳይ ተጨባጭ እርምጃ ነው፡፡
 
ይህ ትብብር ኢትዮጵያ በውቅያኖሶችና በባሕር ቀጠናዎች ላይ ያላትን ብሔራዊ ጥቅም ለማስከበር ለምታደርገው ጥረት ትልቅ አቅም እየፈጠረ ይገኛል፡፡

በኢኮኖሚው ረገድም ግንኙነቱ አዲስ ምዕራፍ ላይ ይገኛል፡፡ በናይሮቢ በተካሄደው የአፍሪካ ፎርዋርድ (Africa Forward Summit) ጉባኤ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተሳትፈው የኢትዮጵያን የአረንጓዴ ኢንዱስትሪ ራዕይና የኃይል ሽግግር አቅርበዋል፡፡
 
በዚሁ ጉባኤ ላይ ፈረንሳይ በአፍሪካ የምታደርገውን የኢኮኖሚ ግንኙነት ከባህላዊ የእርዳታ አቀራረብ በማውጣት፣ በጋራ ኢንቨስትመንትና በምርታማነት ላይ ለማተኮር ያላትን ጽኑ አቋም አንጸባርቃለች፡፡

ኢትዮጵያ ያደረገቻቸውን መጠነ ሰፊ የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች ተከትሎ የፈረንሳይ ኩባንያዎች በታዳሽ ኃይል፣ በግብርና እና በቴክኖሎጂ ዘርፎች ተሳትፏቸውን እያሰፉ ይገኛሉ፡፡
 
ለዚህም የፈረንሳይ ልማት ኤጀንሲ (AFD) ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል መረብ ማዘመኛና ለቀጣናዊ የኃይል ወጪ ንግድ ማሳደጊያ የፈቀደው የ80 ሚሊዮን ዩሮ ብድር በምሳሌነት ይጠቀሳል፡፡
 
ከዚህ በተጨማሪም የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናትን በዘላቂነት ለመጠገንና የከተማዋን ልማት ለመደገፍ የተደረሰው ስምምነት የሁለቱን ሀገራት ዘርፈ ብዙ ትስስር ያሳያል፡፡

በአጠቃላይ የኢትዮጵያና የፈረንሳይ ግንኙነት ታሪካዊ መከባበርንና እውነተኛ ወዳጅነትን መሠረት አድርጎ፣ ዛሬ ላይ አስተማማኝ ወደሆነ ስትራቴጂካዊና ኢኮኖሚያዊ አጋርነት ተሸጋግሯል፡፡
 
በለሚ ታደሰ