Search

ኢትዮጵያ እና ፈረንሳይ፡ ከታሪካዊ ወዳጅነት ወደ ስትራቴጂካዊ የኢኮኖሚ አጋርነት

ሓሙስ ግንቦት 06, 2018 74

ከአንድ ክፍለ ዘመን በላይ የዘለቀው የኢትዮጵያ እና የፈረንሳይ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት አሁን ላይ ወደ ላቀ ስትራቴጂካዊ ትብብር እየተሸጋገረ ይገኛል።

የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በአዲስ አበባ ያደረጉት ጉብኝት ይህንን ታሪካዊ ትስስር ወደ አዲስ ምዕራፍ የሚያሸጋግር ነው፡፡ የንግድ እና የኢንቨስትመንት ግንኙነቱን ይበልጥ ያጠናከረው ሆኗል።

ፈረንሳይ በአውሮፓ ሕብረት ውስጥ ለኢትዮጵያ ቁልፍ የኢኮኖሚ አጋር መሆኗን ተከትሎ ጉብኝቱ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የኢኮኖሚ ትብብር ለማሳደግ ታላቅ ዕድል ፈጥሯል።

ፈረንሳይ በኢትዮጵያ የታዳሽ ኃይል ልማት ላይ እንደ 'EDF' እና 'Meridiam' ካሉ ግዙፍ ኩባንያዎች አማካኝነት ሰፊ ተሳትፎ እያደረገች ትገኛለች።

በተለይም በጂኦ-ተርማል፣ በንፋስ እና የውኃ ኃይል ፕሮጀክቶች ላይ የሚደረገው ድጋፍ ኢትዮጵያ የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ ግቧን እንድታሳካ ከፍተኛ ፋይዳ አለው።

በአሁኑ ወቅት ከ60 በላይ የፈረንሳይ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ተሰማርተው የሚገኙ ሲሆን፣ በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ በመግባት ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ ምርቶችን በማምረት ላይ ይገኛሉ።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ እና የፈረንሳዩ ኤርባስ ኩባንያ የቆየ አጋርነት የሁለቱ ሀገራት የኢኮኖሚ ትብብር ዋነኛ የጀርባ አጥንት ተደርጎ ይወሰዳል።

ይህ አጋርነት አዳዲስ ዘመናዊ አውሮፕላኖችን ከመግዛት ባለፈ በቴክኖሎጂ ሽግግር እና በጥገና ዘርፍ ያለው ትብብር ለኢትዮጵያ አቪዬሽን ኢንዱስትሪ ዕድገት ወሳኝ ሚና እየተጫወተ ይገኛል።

ከዚህ በተጨማሪም በባህል እና ቅርስ ጥበቃ ረገድ የላሊበላ አብያተ ክርስቲያናትን በመጠገን እና ለትውልድ ለማስተላለፍ ፈረንሳይ እያደረገችው ያለው ድጋፍ የሁለቱን ሀገራት ወዳጅነት ልዩ ያደርገዋል።

ኢትዮጵያ አጠቃላይ የኢኮኖሚ ማሻሻያ በምታደርግበት በዚህ ወቅት የፈረንሳይ አጋርነት ተመራጭ እና ተፈላጊ ነው።

በተለይም ኢትዮጵያ ከዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት (IMF) ጋር የምታደርገው ድርድር እንዲሳካ እና በፓሪስ ክለብ በኩል የሚከናወኑ የዕዳ ማሻሻያ ሂደቶች ውጤታማ እንዲሆኑ ፈረንሳይ የምታደርገው ዲፕሎማሲያዊ እና ቴክኒካዊ ድጋፍ የሚደነቅ ነው።

የኢትዮጵያ ቡና እና ሌሎች የግብርና ምርቶች ጥራታቸው ተጠብቆ ወደ ፈረንሳይ ገበያ እንዲላኩ የሚደረገው የሙያ ድጋፍም የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ ሌላኛው የትብብር መስክ ነው።

የፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ጉብኝት በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ግንኙነት ወደ ላቀ የንግድ አጋርነት የቀየረው ሲሆን በተለይም በግል ዘርፍ ኢንቨስትመንት፣ በታዳሽ ኃይል እና በፋይናንስ ዘርፍ የሚደረጉ አዳዲስ ስምምነቶች ኢትዮጵያ የጀመረችውን የኢኮኖሚ ብልጽግና ጉዞ የሚያፋጥኑ ሞተሮች እንደሚሆኑ ይታመናል።


በሔዋን ጌታቸው