Search

የኢትዮጵያና የተባበሩት መንግሥታት፡ የታሪክ ትላንትና የለውጥ ዛሬ

ሓሙስ ግንቦት 06, 2018 46

በዓለም አቀፍ መድረክ ላይ የአንድ አገር ገጽታ የሚለካው በቆዳ ስፋቷ ወይም በሕዝብ ብዛቷ ብቻ ሳይሆን፣ ለዓለም አቀፋዊ እሴቶች በምትከፍለው መስዋዕትነትና በምትከተለው የፀና የዲፕሎማሲ መርህ ጭምር ነው። በዚህ ረገድ የኢትዮጵያና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተ.መ.ድ) ግንኙነት በታሪክ ማኅደር ውስጥ በደማቅ ቀለም የሚጻፍ ጥልቅ ትርክት ነው።

ኢትዮጵያ በአውሮፓውያኑ 1945 የድርጅቱን ቻርተር በፊርማዋ ካጸደቁ 51 መስራች አገራት መካከል አንዷ መሆኗ ብቻ ሳይሆን፣ የድርጅቱ መንፈስ በአፍሪካ ምድር ሥር እንዲሰድ ያደረገች ቀዳሚ የዲፕሎማሲ መሐንዲስ ናት። ይህ ለስምንት አስርት ዓመታት የዘለቀ አጋርነት፣ ከወረቀት ላይ ስምምነት አልፎ በኮሪያ ተራራዎች ላይ በፈሰሰ ደም፣ በአቢዬ በረሃዎች በተረጋገጠ ሰላምና በአዲስ አበባ ጎዳናዎች ላይ በታየ የዲፕሎማሲ ማዕከልነት ተገንብቷል።

የኢትዮጵያ ባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲ (Multilateralism) ጉዞ አልጋ በአልጋ አልነበረም። መስከረም 28 ቀን 1923 የመንግሥታቱ ማኅበርን ስትቀላቀል፣ ዓላማዋ ሉዓላዊነቷን በሕግ ጥላ ሥር ለመጠበቅ ነበር። ሆኖም በአውሮፓውያኑ 1935 የፋሺስት ጣሊያን ወረራ ሲፈጸም ማኅበሩ የጋራ ደህንነትን ለማስከበር አለመቻሉ፣ ለዓለም አቀፍ ተቋማት ትልቅ የሞራልና የፖለቲካ ፈተና ሆኖ አልፏል። አፄ ኃይለ ሥላሴ በጄኔቫ መድረክ ያደረጉት ንግግር የኢትዮጵያን ድምፅ ብቻ ሳይሆን፣ የፍትሕን መጓደል ለዓለም ያሳየ መራራ የታሪክ አጋጣሚ ነበር።

ይህ የታሪክ ጠባሳ ኢትዮጵያ በ1945 የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሲመሠረት በርትታ እንድትሳተፍ አድርጓታል። "ዳግም የጋራ ደህንነት ሥርዓት አይውደቅ" በሚል ጽኑ አቋም የድርጅቱ መሃንዲስ ሆና ብቅ አለች። ይህ ታሪካዊ ሚና ኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲዋን ከሉዓላዊ እኩልነት፣ ከግዛት አንድነት እና ከዓለም አቀፍ ትብብር መርሆዎች ጋር እንድታቀናጅ አስችሏታል።

ኢትዮጵያ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ያላት ታማኝነት በቃላት ብቻ ሳይሆን በተግባር የተፈተነ ነው። ከ1951ዱ የኮሪያ ጦርነት ጀምሮ የኢትዮጵያ ሠራዊት በተባበሩት መንግሥታት ሰማያዊ ኮፍያ ሥር የማይረሳ ታሪክ ሰርቷል። የቃኘው ሻለቃ በኮሪያ ልሳነ ምድር ያሳየው ጀግንነትና ዲሲፕሊን፣ ዛሬም ድረስ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚጠቀስ የሰላም ተልዕኮ ተምሳሌት ነው።

ዛሬ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የሰላም አስከባሪ ሠራዊት ከሚያዋጡ አምስት ቀዳሚ አገራት ተርታ ትመደባለች። ሰራዊቷ በሩዋንዳ፣ በቡሩንዲ፣ በላይቤሪያ፣ በኮትዲቩዋር፣ በሱዳን፣ በደቡብ ሱዳን እና በሶማሊያ በተከናወኑ ውስብስብ ተልዕኮዎች ውስጥ ተሳትፏል። በአውሮፓውያኑ 2026 ኢትዮጵያ በተለያዩ ተልዕኮዎች ከ8,000 በላይ ንቁ የሰላም አስከባሪዎችን እያሳተፈች ትገኛለች።

በተለይም በአቢዬ (UNISFA) የተሰማራው ኃይል መጀመሪያ ላይ ሙሉ በሙሉ በኢትዮጵያ ወታደሮች መዋቀሩ፣ በካርቱም እና በጁባ መንግስታት ዘንድ ያላትን ከፍተኛ ተዓማኒነት የሚያሳይ ነው። የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪዎች ከወታደራዊ ግዳጅ ባሻገር በትምህርት ቤቶች፣ በጤና ክሊኒኮችና በመሠረተ ልማት ግንባታዎች ላይ በመሳተፍ "ሰውን ማዕከል ያደረገ" የጸጥታ አቀራረብ በመፍጠር ረገድ ቀዳሚ ናቸው።

የአዲስ አበባ ከተማ ወደ ዓለም አቀፍ የዲፕሎማሲ ማዕከልነት ማደግ ከኢትዮጵያ እና ተ.መ.ድ አጋርነት ጋር የተቆራኘ ነው ። እ.ኤ.አ በ1958 የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን (UNECA) መመስረት ከተማዋን የአህጉራዊ ልማት አስተዳደራዊና ፖለቲካዊ ማዕከል አድርጓታል። ዛሬ ከተማዋ ከ100 በላይ ኤምባሲዎችንና ዓለም አቀፍ ተልዕኮዎችን በማስተናገድ "የአፍሪካ የዲፕሎማሲ ዋና ከተማ" ተብላ ትጠራለች።

የUNECA እና የአፍሪካ ሕብረት መቀመጫዎች በአንድ ከተማ መሆኑ፣ የተ.መ.ድን የ2030 የዘላቂ ልማት ግቦች ከአፍሪካ ሕብረት የ2063 አጀንዳ ጋር ለማቀናጀት አመቺ ሁኔታ ፈጥሯል። ይህ ቅንጅት ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍና በአህጉራዊ የአስተዳደር መዋቅሮች መካከል ከፍተኛ ትብብር እንዲኖር በማድረግ ረገድ ያላትን ቁልፍ ሚና ያጎላል።

እ.ኤ.አ ግንቦት 13 ቀን 2026 የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶንዮ ጉቴሬዝ በአዲስ አበባ ያደረጉት ጉብኝት የኢትዮጵያ እና የተ.መ.ድ ግንኙነት የደረሰበትን ከፍታ የሚያሳይ ነው ። ጉብኝቱ የድርጅቱን 80ኛ ዓመት የምስረታ በዓል ምክንያት በማድረግ የተከናወነ ሲሆን፣ ጉቴሬዝ ኢትዮጵያ ለባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲ ያላትን አመራር እና ቀጣይነት ያለው ቁርጠኝነት አድንቀዋል።

በጉብኝቱ ወቅት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና በዋና ጸሐፊው አማካኝነት "በሰላም አብሮ ለመኖር" በሚል መሪ ቃል የመታሰቢያ ቴምብሮች በብሔራዊ ቤተ መንግስት ተመርቀዋል ። እነዚህ ቴምብሮች በ192 አገራት የሚሰራጩ ሲሆን፣ የኢትዮጵያን ታሪካዊ ሚና ለዓለም የሚያስተዋውቁና የወደፊቱን የትብብር አቅጣጫ የሚጠቁሙ ናቸው።

በዚህ ታሪካዊ ጉብኝት ወቅት ጉቴሬዝ ያነሱት ሌላው ቁልፍ ጉዳይ የዓለም አቀፍ ተቋማት ሪፎርም ነው ። አፍሪካ በጸጥታው ምክር ቤት ቋሚ መቀመጫ እንዳይኖራት መደረጉ "ታሪካዊ ኢ-ፍትሃዊነት" መሆኑን በመግለጽ፣ ምክር ቤቱ የ21ኛውን ክፍለ ዘመን ነባራዊ ሁኔታ እንዲያንጸባርቅ ኢትዮጵያና አፍሪካ የሚያቀርቡትን የሪፎርም ጥያቄ በይፋ ደግፈዋል።

በኢትዮጵያ እና በተ.መ.ድ መካከል ያለው የኢኮኖሚ ግንኙነት ከሰብአዊ ድጋፍ ባለፈ ወደ ስትራቴጂካዊ የልማት አጋርነት ተሸጋግሯል ። ሰኔ 20 ቀን 2025 የተፈረመው የ2025-2030 የዘላቂ ልማት የትብብር ማዕቀፍ (UNSDCF) ለቀጣዮቹ አምስት ዓመታት 6.5 ቢሊዮን ዶላር በጀት ይዟል። ይህ ማዕቀፍ የኢትዮጵያን የ10 ዓመት የልማት ዕቅድ ለማሳካትና የአንድ ሰው ገቢን ወደ 1,560 ዶላር ለማሳደግ ያለመ ነው።

የአሁኑ መንግሥት ለዲፕሎማሲው መስክ የሰጠው ትኩረት ከአህጉራዊ መሪነት ባለፈ፣ ኢትዮጵያን የዓለም መዳረሻ ለማድረግ ያለመ ነው። አዲስ አበባን "የአፍሪካ የዲፕሎማሲ ዋና ከተማ" ከሚለው ስያሜ በላይ፣ የዓለም መስህብና የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ የተከናወኑት የኮሪደር ልማትና የውበት ግንባታ ሥራዎች እጅግ አስገራሚ ናቸው። ከተማዋን ወደ ዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍ ያደረጉት እንደ አንድነት፣ ወዳጅነትና እንጦጦ ፓርኮች ያሉ ፕሮጀክቶች፣ እንዲሁም የሳይንስ ሙዚየም ግንባታ አዲስ አበባን በዲፕሎማቶችና በጎብኚዎች ዓይን አዲስና ማራኪ አድርጓታል።

ይህ የአዲስ አበባ ሽግግር ለዲፕሎማሲው ስኬት ትልቅ ግብዓት ሆኗል። ዋና ከተማዋ አሁን ላይ ከ100 በላይ ኤምባሲዎችንና የዓለም አቀፍ ድርጅቶችን መቀመጫ ብቻ ሳይሆን፣ ዓለም አቀፍ ጉባኤዎችና ስብሰባዎች በታላቅ ድምቀት የሚስተናገዱባት ማራኪ መድረክ ሆናለች። በተለይም እ.ኤ.አ ግንቦት 13 ቀን 2026 የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶንዮ ጉቴሬዝ በአዲስ አበባ ያደረጉት ታሪካዊ ጉብኝት፣ የከተማዋን ውበትና የዲፕሎማሲያዊ አቅሟን ለዓለም የመሰከረ ክስተት ነው።

በአዶኒያስ ወ/አረጋይ