የኢትዮጵያ የባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲ እና ለጋራ ደኅንነት ሥርዓት ያላት ፅኑ ቁርጠኝነት ረጅም ታሪካዊ መሠረት አለው።
ኢትዮጵያ ከአንደኛው የዓለም ጦርነት ማብቃት በኋላ በመንግሥታት ማኅበር (League of Nations) ውስጥ ቀዳሚና ብቸኛዋ አፍሪካዊት አባል ሀገር በመሆን የሕግ የበላይነት እንዲከበር የበኩሏን ሚና ተወጥታለች።
ይሁን እንጂ ማኅበሩ የጋራ ደኅንነትን የመጠበቅ ኃላፊነቱን መወጣት ባለመቻሉ፣ በተለይም በኢትዮጵያ ላይ የተሰነዘረውን የፋሽስት ጣሊያንን ወረራ መግታት ሲሳነው በትልቅ መዋቅራዊ ውድቀት ተፈትኗል። ይህ ውድቀት ዓለምን ወደ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት አዘቅት የከተተ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ ቀድማ ያሰማችው ማስጠንቀቂያም ዓለም አቀፍ ተቋማት ጠንካራና ፍትሐዊ መሆን እንዳለባቸው ትልቅ የታሪክ ትምህርት ጥሎ አልፏል።
እ.አ.አ በ1945 የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ሲመሠረት፣ ኢትዮጵያ ቻርተሩን ከፈረሙ 51 ቀዳሚ አገራት አንዷ በመሆን ለዓለም አቀፍ ሰላም አዲስ ምዕራፍ ከፋች ሆናለች። ይህንን ታሪካዊ ኃላፊነቷን በተግባር ለመወጣትም ከ1950ዎቹ የኮሪያ ጦርነት ጀምሮ በሰላም ማስከበር ተልዕኮ ላይ ንቁ ተሳትፎ ማድረግ ጀምራለች።
በኮሪያ ምድር የድርጅቱን ጥሪ ተቀብላ ወታደር የላከች ብቸኛ አፍሪካዊት ሀገር ስትሆን ከክብር ዘበኛ የተውጣጣው ዝነኛው "ቃኘው ሻለቃ" በተመድ ዓርማ ሥር በፈጸመው ተጋድሎ ከፍተኛ ወታደራዊ ዝናን አትርፏል።
በታሪክ አንድም ወታደር ሳይማረክበት እና የሞተ አጋሩን የጦር ሜዳ ላይ ጥሎ ሳይወጣ ተልዕኮውን የፈጸመው ይህ ኃይል፣ ለኢትዮጵያ የሰላም ማስከበር ስኬት ጽኑ መሠረት ጥሏል።
ይህንን ተከትሎ በ1960ዎቹ በኮንጎ፣ በ1990ዎቹ እና በ2000ዎቹ መጀመሪያ በሩዋንዳ፣ በላይቤሪያ እንዲሁም በቡሩንዲ በተካሄዱ ተልዕኮዎች ላይ በመሳተፍ ግጭቶችን በማረጋጋት ረገድ ውጤታማ ተግባራትን አከናውናለች።
በተመሳሳይ በቀጣናው ሰላም ለማምጣት በሶማሊያ በተሰማራው የአፍሪካ ሕብረት ተልዕኮ ውስጥ ከፍተኛ መስዋዕትነት በመክፈል የሽብር ስጋትን በመቀነስ ረገድ የማይተካ ሚና እየተጫወተች ትገኛለች።
የኢትዮጵያ ስኬታማ የሰላም ማስከበር ተልዕኮ በቅርብ ጊዜያት በዳርፉር፣ በአብዬ እና በደቡብ ሱዳን ይበልጥ ጎልቶ ወጥቷል።
በተለይም በተባበሩት መንግሥታት የአብዬ ጊዜያዊ የጸጥታ ኃይል (UNISFA) ውስጥ የተጫወተችው ሚና ልዩ የታሪክ ቦታ አለው።
ተፋላሚዎቹ የካርቱም እና የጁባ ወገኖች ሙሉ እምነታቸውን በኢትዮጵያ ላይ በመጣል፣ የሰላም አስከባሪው ኃይል ሙሉ በሙሉ ከኢትዮጵያ ብቻ እንዲመጣ በአዲስ አበባ ስምምነት ላይ በግልጽ ጠይቀዋል።
ይህም ሀገራችን በሺዎች የሚቆጠሩ ወታደራዊና የፖሊስ አባላትን በአስደናቂ ፍጥነት በማሰማራት ንጹሀንን ከጥቃት እንድትጠብቅ አስችሏታል። ከዚህ በተጨማሪ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን የሴት ሰላም አስከባሪዎችን በማሰማራት ረገድ ያሳየችው አርአያነት በተመድ ዘንድ ከፍተኛ አድናቆትን አትርፎላታል።
እስካሁን ከ80 ሺህ በላይ የሠራዊት እና የፖሊስ አባላትን በተለያዩ ዓለም አቀፍ ተልዕኮዎች ላይ ያሰማራችው ኢትዮጵያ፣ ለዓለም ሰላም ያላትን ፅኑ አቋም በደም እና በከባድ መስዋዕትነት በተግባር አረጋግጣለች።
ይህ ግዙፍ አስተዋጽኦ ሀገራችን በተመድ የፀጥታው ምክር ቤት ላይ መዋቅራዊ ማሻሻያ እንዲደረግ ለምታቀርበው ጥሪ የሞራል የበላይነት ሰጥቷታል።
በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ አፍሪካ በምክር ቤቱ ውስጥ ተመጣጣኝ ድምፅ እና ፍትሐዊ ውክልና እንዲኖራት በጽኑ እየተሟገተች ነው።
ሀገራችን የ"እዙልዊኒ"ስምምነት (Ezulwini Consensus) በመባል የሚታወቀውን የአፍሪካ የጋራ አቋምን በማራመድ፣ ቢያንስ ድምፅን በድምፅ የመሻር (Veto Power) ሥልጣን ያላቸው ሁለት ቋሚ መቀመጫዎች እና አምስት ተለዋጭ መቀመጫዎች ለአፍሪካ እንዲሰጡ በተለያዩ መድረኮች ጥሪዋን እያቀረበች ትገኛለች።
የኢትዮጵያ አካታች ዲፕሎማሲ የዓለም አቀፍ ተቋማትን ሕጋዊነትና ተዓማኒነት ከማሳደግ ባሻገር፣ ታሪካዊ የፍትሕ መጓደሎችን ለማረም ያለመ ነው።
የምክር ቤቱ መዋቅር የ1945ቱን የጂኦፖለቲካ ቅሪት ብቻ ሳይሆን፣ የዛሬውን ተጨባጭ ዓለም አቀፋዊ እውነታ በሚያጸባርቅ መልኩ መለወጥ እንዳለበትም ፅኑ እምነቷ ነው።
በመሆኑም ኢትዮጵያ ለዓለም ሰላም የምታበረክተው አስተዋጽኦ ባለፉት ዘመናት የተመዘገበ የታሪክ ውርስ ብቻ ሳይሆን ዛሬም በግጭት ቀጠናዎች ውስጥ በሚፈስ የጀግኖች ደምና መስዋዕትነት የሚረጋገጥ ሕያው እውነት ነው።
ይህ ተሳትፎ ኢትዮጵያ በባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲ መድረክ ያላትን ተሰሚነት ከፍ ከማድረጉም ባለፈ፣ እንደ አፍሪካ ቀንድ ባሉ ቀጠናዎች ውስጥ እንደ ዋነኛ የሰላም መልሕቅ እንድትታይ አድርጓታል። ወደፊትም በዓለም አቀፍ ደረጃ ፍትሐዊ ውክልና እንዲሰፍን የምታደርገው ተሟጋችነት እና በሰላም ማስከበር ረገድ የምታሳየው ፅኑ ቁርጠኝነት፣ የኢትዮጵያዊነትን ታላቅ አሻራ በዓለም ዲፕሎማሲ መድረክ ላይ በደመቀ ሁኔታ የሚያስቀጥል ስትራቴጂካዊ ተልዕኮ ነው።
በለሚ ታደሰ