በመቅደላ ጦርነት ወቅት ተዘርፈው ወደ እንግሊዝ ተወስደው የነበሩት የንጉሠ ነገሥት አፄ ቴዎድሮስ የፀጉር ቁንዳል፣ የልብስ ቁራጮች እና የወርቅ አምባር ከ158 ዓመታት በኋላ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰዋል።
ቅርሶቹን ከእንግሊዝ ይዘው የመጡት የንግሥቲቱ ቤተሰብ ሙዚየም ኃላፊ ሮቢን ጃክሰን (ዶ/ር) እና የኢትዮጵያ ቅርስ አስመላሽ ኮሚቴ አባልና ተመራማሪው አሉላ ፓንክረስት (ዶ/ር) ናቸው።
የኢትዮጵያ ቅርስ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው እና የኢትዮጵያ አርበኞች ማኅበር አባላት በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በመገኘት አቀባበል አድርገዋል።
ሮቢን ጃክሰን (ዶ/ር) እና አሉላ ፓንክረስት (ዶ/ር) ቅርሶቹ ከረጅም ዓመታት በኋላ ወደ ሀገራቸው የተመለሱበት ቀን በመሆኑልዩ ቀን ነው ብለዋል።
የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው በበኩላቸው፣ በተለያዩ ምክንያቶች ከሀገር የወጡ ታሪካዊ ቅርሶችን የመመለስ ሥራ በትኩረት እየተሠራ መሆኑን ገልጸው፣ ዘንድሮ አመርቂ ሥራ የተሠራበትና ትልቅ የዲፕሎማሲ ስኬት የተገኘበት ዓመት መሆኑን አብራርተዋል።
የቅርሶቹ ይፋዊ የርክክብ ሥነ-ሥርዓት ነገ ግንቦት 7 ቀን 2018 ዓ.ም በባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ የሚከናወን ይሆናል።