Search

የባሕር በራችን፡ የተቀማው ትርታችን እና የትውልዱ ትንሣኤ

ሓሙስ ግንቦት 06, 2018 85

ኢትዮጵያ በታሪኳ ቀዳሚ ከሆነችባቸው ታላላቅ መገለጫዎች አንዱና ዋነኛው የቀይ ባሕር ሥልጣኔ ባለቤትነቷ ነው። የኢትዮጵያ የየብስ ተከል  ሆኖ መቅረት ተፈጥሯዊ ዕጣ ፈንታዋ በፍጹም አይደለም። ይልቁንም በታሪካዊ ጠላቶቿና በቅኝ ገዥዎች የረጅም ዘመን የሴራ ድር የተፈበረከ፣ አገሪቱን ከዕድገት ለማሰር የተሸረበ አርቲፊሻል ኩነት መሆኑን የታሪክና የሕግ ምሁራን በአንድ ድምፅ ይስማማሉ።

የኢትዮጵያ መንግሥታዊ ህልውና፣ ክብር እና ብልጽግና ከቀይ ባሕር ጋር የነበረው ቁርኝት እንደ ዕትብት የማይነጣጠል እንደነበር በጥንታዊ የግሪክ፣ የሮማውያንና የፋርስ የታሪክ ሰነዶች በጉልህ ተረጋግጧል። ከ1ኛው እስከ 9ኛው ክፍለ ዘመን ድረስ የነበረው ታላቁ የአክሱም ግዛት፣ በዓለም ላይ ከነበሩ አራት ታላላቅ ኃይሎች አንዱ ሊሆን የቻለው የቀይ ባሕርን የንግድ መስመሮች በበላይነት በመቆጣጠሩ ነበር።

በወቅቱ አዱሊስ የዓለም አቀፍ ንግድ የልብ ትርታ፣ ወሳኝ የኢኮኖሚና የስትራቴጂ ማዕከል ነበረች። አገራችን የራሷን ሳንቲም በማተም እስከ ሕንድና ሩቅ ምሥራቅ ድረስ ግዙፍ የባሕር ንግድ ታካሄድ የነበረች ታላቅ የባሕር ኃይል ነበረች። በሰሜን ኢትዮጵያ የነበረው “ ባሕረ ምድሪ”  ግዛት፣ በቀጥታ በኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥታት ሥር የነበረ ግዛት ነው። 


ይህ አስተዳደራዊ መዋቅር የባሕር ጠረፋችንን ደህንነት በንቃት የሚጠብቅ፣ ታላቁን የ“ባሕረ ነጋሽ” ትውፊት ያቆመ እና ሉዓላዊነታችንን በውኃ ላይ ያረጋገጠ የኩራታችን ምንጭ ነበር።ሆኖም ይህን ታላቅነት ለማዳከም ጠላቶቻችን አይናቸውን አላረፉም። ኢትዮጵያን ከባሕር ነጥሎ የማዳከም ስልታዊ ሴራ ለዘመናት ሲሰራጭ ቆይቷል።

በ16ኛው ክፍለ ዘመን የኦቶማን ግዛት የምጽዋን ወደብ በመቆጣጠር ኢትዮጵያን ከቀጥታ የባሕር ግንኙነት ለመቁረጥ የሞት ሽረት ጥረት አድርጓል። ይሁን እንጂ አባቶቻችን ከውስጥ በነበሩ የንግድ መተላለፊያዎችና በወኪሎቻቸው አማካኝነት ግንኙነታቸውን ሳያቋርጡ አቆይተዋል።ፈተናው ግን በዚህ አላበቃም።

በ1880ዎቹ የአውሮፓ ኃይሎች አፍሪካን እንደ ቅርጫ ሥጋ ለመቀራመት ሲነሱ፣ እንግሊዝ፣ ፈረንሳይ እና ጣሊያን ኢትዮጵያን ከባሕር ለማራቅ በጋራና በተናጠል ተረባርበዋል።

በተለይም በ1881 ዓ.ም የተፈረመው የውጫሌ ውል 17ኛው አንቀጽ ላይ ጣሊያን የፈጠረችው የትርጉም ማጭበርበር፣ ኢትዮጵያን የጣሊያን ሞግዚት በማድረግ ባሕር ዳርቻዋን ሙሉ በሙሉ ለመንጠቅ የታለመ እኩይ ሴራ ነበር።

ምንም እንኳን ጀግናው የኢትዮጵያ ሕዝብ በ1888 ዓ.ም በተካሄደው የአድዋ ጦርነት ጣሊያንን አይቀጡ ቅጣት ቀጥቶ ሉዓላዊነቱን በደም ቢያስከብርም፣ የቅኝ ገዥዎች ተንኮል ግን አላረፈም። በ1892፣ በ1894 እና በ1900 ዓ.ም በተደረጉ ኢ-ፍትሃዊ ውሎች፣ ኢትዮጵያ በቀጥታ ባሕር ዳርቻ እንዳይኖራት የሚያደርጉ የድንበር ድልድሎችን በአስገዳጅ ሁኔታ እንድትቀበል ተደርጓል።

የዘመናዊቷ ኢትዮጵያ የባሕር በር አልባነት ትልቁ ማሳረጊያ ሆኖ የተመዘገበው በ1985 ዓ.ም የኤርትራን መገንጠል ተከትሎ የመጣው ክስተት ነው። ይህ ታሪካዊ ስህተት በብዙ ምሁራን ዘንድ “በታሪካዊ ጠላቶች በጥንቃቄ የተቀነባበረ የፖለቲካ ድራማ” ተብሎ በቁጭት ይነሳል።

የቀድሞው የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሐፊ ቡትሮስ ቡትሮስ ጋሊ የዚህ አስከፊ ድራማ ዋነኛ ደራሲ እንደሆኑና፣ በወቅቱ የነበሩ የኢትዮጵያ መሪዎች ደግሞ የዚህ ታሪካዊ ስህተት ፈጻሚዎች እንደነበሩ የታሪክ መረጃዎች ያሳያሉ። 

የኢትዮጵያ ሕዝብ ድምፅ ሳይሰጥበትና የባሕር በርን ሕልውና ግምት ውስጥ ሳይገባ የተደረገው ይህ የችኮላ ክፍፍል፣ ኢትዮጵያን በአንድ ጀምበር ከባሕር ኃይል ባለቤትነት አውርዶ፣ በዓለማችን ትልቋ የየብስ ተከል አገር እንድትሆን ፈርዶባታል። 

የዚህ የየብስ ተከልነት ጂኦግራፊያዊ እስራት በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ላይ እያደረሰ ያለው ደም መፍሰስ ቃላት ከሚገልጹት በላይ ዘግናኝ ነው።

በባሕር በር አልባነት ምክንያት ብቻ አገራችን በየዓመቱ የምታጣው ሀብት የ130 ሚሊዮን ሕዝብን የእድገት ተስፋ የሚያጨልም ነው። ምሁራዊ ትንተናዎች እንደሚያሳዩት፣ ኢትዮጵያ በየዓመቱ ከ19 ቢሊዮን እስከ 31 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት የጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት (GDP) ኪሳራ ይገጥማታል።

ይህ አሃዝ ከጠቅላላ ምርታችን ከ13 በመቶ እስከ 23 በመቶ የሚደርስ ግዙፍ ድርሻ ያለው ነው። ከዚህም ባሻገር፣ ለወደብ ኪራይና ለአገልግሎት ክፍያ ብቻ በየዓመቱ እስከ 2 ቢሊዮን ዶላር እንገብራለን።

ይህ አስደንጋጭ አሃዝ ኢትዮጵያ በየዓመቱ ለውጭ ዕዳ ከምትከፍለው ክፍያ በ193 በመቶ የሚበልጥ መሆኑ ሲታሰብ፣ የጉዳቱን ጥልቀት እና እዳችንን ያሳብቃል። 

የሎጂስቲክስ ጫናውም ቢሆን ሌላው የኢኮኖሚ ማነቆያችን ነው። በዓለም አቀፍ ደረጃ የሎጂስቲክስ ወጪ በአማካይ ከ8 እስከ 12 በመቶ ሲሆን፣ በኢትዮጵያ ግን የምርት ዋጋን ከ20 እስከ 30 በመቶ ያህል እንዲንር አድርጎታል።

ይህ ልዩነት በኢትዮጵያ ንግድ ላይ የተጫነ ቋሚና አላስፈላጊ ቀረጥ ሆኗል። በአጠቃላይ ይህ የታሪክና "የጂኦግራፊ እስራት" ኢትዮጵያ በየዓመቱ ከ3.7 ቢሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ እንድታጣ እያደረጋት ነው።
ለድህነት ቅነሳ፣ ለትምህርት፣ ለጤና እና ለመሠረተ ልማት መዋል የነበረበት ይህ ሁሉ ግዙፍ ዐቅም፣ በባሕር በር አልባነታችን ምክንያት ገደል እየገባ ይገኛል። ይሁን እንጂ፣ ኢትዮጵያን ከባሕር ነጥሎ በድህነት ለማቆየት የተሰሩት እነዚህ ሁሉ የዘመናት ሴራዎች፣ የሕዝቡን የማይበገር መንፈስ በዘላቂነት ሊሰብሩት አልቻሉም።

ለዚህም ታሪካዊ ቀጣይነታችን ትልቁ ምስክር ነው። በ1945 ዓ.ም የኤርትራና የኢትዮጵያ ፌዴሬሽን በተመሠረተ ጊዜ፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኢትዮጵያን ሕጋዊ የወደብ ጥያቄ በመቀበል ውሳኔ 390 (V) ማሳለፉ፣ የታፈነው የአክሱም ዘመን መብታችን መቼም ቢሆን እንደማይሞት ያሳየ ክስተት ነበር።

ዛሬ ላይ ደግሞ ተስፋው ይበልጥ ደምቋል። በአሁኑ ወቅት ከሕዝባችን 65 በመቶ በላይ የሚሆነው ወጣት ትውልድ የባሕር በር ጥያቄን እንደ ተራ የፖለቲካ ፍላጎት ሳይሆን፣ እንደ "ብሔራዊ ሕልውና" (Existential Issue) ወስዶታል። 

ይህ ትውልድ ከታሪካዊ እስራቱ ለመውጣት ቆርጦ ተነስቷል። የታሪክ ሚዛን መስተካከሉ አይቀሬ ነው። ኢትዮጵያ የየብስ ተከል ሆና እንድትቀጥል ለዘመናት የተሸረቡ ሴራዎች፣ የ130 ሚሊዮን ሕዝብን የዕድገት ጥማት፣ ፍላጎትና ታሪካዊ መብት ከቶውንም ሊገቱት አይችሉም። 

የባሕር በር ጥያቄያችን የትውልድ የህልውና፣ የነፃነትና የክብር ጥያቄ ነው። ምሁራዊ መረጃዎችና የሕግ ዐውዶች እንደሚያረጋግጡት፣ ኢትዮጵያ ያላት ታሪካዊና ሕጋዊ መብት በጊዜያዊ የፖለቲካ ስምምነቶች ተቀብሮ የሚቀር አይደለም። 

አዲሱ ትውልድ ይህንን ታሪካዊ ኢ-ፍትሃዊነት በጽናት በመቀየር፣ የአባቶቹን የባሕር ኃይል ክብር ለመመለስና አገሩን ከጂኦግራፊያዊ የፖለቲካ እስራት ነፃ ለማውጣት መነሳቱ፣ ኢትዮጵያ በቅርብ ጊዜ ውስጥ ወደ ተፈጥሯዊ የባሕር ባለቤትነቷ እንደምትመለስ የሚያበስር የማይታበል ዕውነት ነው።

 

በአዶኒያስ ወ/አረጋይ