ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የኢትዮጵያ አየር መንገድ 24ኛ የሀገር ውስጥ መዳረሻ የሆነውን አዲሱን የነገሌ ቦረና ገዳ አውሮፕላን ማረፊያ ዛሬ በይፋ መርቀው ለአገልግሎት ክፍት አድርገዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት አውሮፕላን ማረፊያው እንደ ቦይንግ 737 ማክስ ያሉ ግዙፍ እና ዘመናዊ አውሮፕላኖችን የማስተናገድ አቅም እንዳለው ገልጸዋል።
ተቋሙ በሳምንት ሦስት በረራዎችን በማስተናገድ የአካባቢውን እንዲሁም ድንበር ተሻጋሪ የንግድ ልውውጥን እና ቱሪዝምን የማሳደግ ራዕይ ሰንቆ ወደ ስራ መግባቱንም አስታውቀዋል።
በምስራቅ ቦረና ዞን የተገነባው ይኸው ማረፊያ ለአገልግሎት ክፍት መሆኑ፣ ምቹ፣ ፈጣን እና ቀልጣፋ የትራንስፖርት አገልግሎት ለማግኘት እንደሚያስችላቸው የዞኑ ነዋሪዎች ተናግረዋል።
አስተያየታቸውን የሰጡት የአካባቢው ነዋሪዎች፣ ፕሮጀክቱ በየብስ ትራንስፖርት ረጅም ጉዞ ምክንያት ይደርስ የነበረውን እንግልት በእጅጉ እንደሚያቃልል ገልጸዋል።
ዞኑ በእንስሳት ሀብት እና ስንዴ ምርት የሚታወቅ በመሆኑ ምርትን በፍጥነት በማጓጓዝ በኩል ያጋጥም የነበረውን የትራንስፖርት እጥረት በመፍታት የንግድ ዝውውርን እንደሚያቀላጥፍ ነዋሪዎቹ እምነታቸውን አጋርተዋል።
በተጨማሪም የነገሌ ቦረና ከተማን የንግድ እና የቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ፣ ለወጣቶች ሰፊ የሥራ ዕድል ለመፍጠር፣ እንዲሁም ባለሀብቶች በቀላሉ ወደ ዞኑ ገብተው ኢንቨስት እንዲያደርጉ ተጨማሪ አቅም እንደሚሆን አብራርተዋል።
ይህም መንግሥት ለአርብቶ አደሩ አካባቢ የሰጠውን ትኩረት እና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት በተግባር ያረጋገጠ መሆኑን መጥቀሳቸውን ኢዜአ ዘግቧል።