የቦረና ሕዝብ ለሀገራዊ አንድነት እና ለሀገር ደኅንነት ጥበቃ ያበረከተው አስተዋጽኦ የላቀ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዛሬው ዕለት የተመረቀውን የቦረና ነጌሌ ገዳ አውሮፕላን ማረፊያን ባስመረቁበት ወቅት ባደረጉት ንግግር ዛሬ የተመረቀው የአውሮፕላን ማረፊያ ለቦረና ሕዝብ ታላቅ በረከት እና ስጦታ ቢሆንም፣ ሕዝቡ ካለው ጥንካሬ እና ካበረከተው ታሪካዊ አስተዋጽኦ አንጻር ገና ብዙ ሊሠራለት እንደሚገባ ተናግረዋል።
ሕዝቡ ለረጅም ዓመታት በረሃብ እና በጥም ውስጥ ቢኖርም፣ ጥርሱን ነክሶ ማንነቱን፣ ባህሉን፣ ቋንቋውን እና የገዳ ሥርዓቱን ጠብቆ ማቆየቱን እንዲሁም የሀገራችንን ደኅንነት ሲጠብቅ መኖሩን አውስተው፤ ለቦረና፣ ለጉጂ እና ለባሌ ሕዝቦች ላቅ ያለ ምስጋና አቅርበዋል።
በአካባቢው የመሠረተ ልማት አለመኖር ቀደም ሲል ባሌ፣ ቦረና፣ ጉጂ እና ቱለማ እርስ በርሳቸው እንደ ባዕድ እንዲተያዩ እና እንዲበታተኑ ምክንያት ሆኖ መቆየቱን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የመሠረተ ልማት መዘርጋት ሕዝብን የማገናኘት፣ ንግድን የማሳለጥ እና የተረሱ ባህላዊ እሴቶችን የማደስ አቅም እንዳለው አስገንዝበዋል።
አሁን በተገነባው የቦረና ገዳ አውሮፕላን ማረፊያ አማካኝነት ቀደም ሲል የነበረው የመገናኛ ርቀት በከፍተኛ ደረጃ እንደሚሰበሰብ እና ከነገሌ ተነሥቶ በ1 ሰዓት ውስጥ ወደ ነቀምቴ፣ ጅማ እና ቢሾፍቱ መጓዝ እንደሚቻል ጠቁመዋል።
ይህም ግንኙነትን እና ንግድን ከማጠናከር ባለፈ ባህል እና ማንነትን ለትውልድ ለማስተላለፍ ይረዳል ብለዋል።
መንግሥትም በሁሉም የኢትዮጵያ አቅጣጫዎች ሳያደላ የአውሮፕላን ማረፊያ አውታረ መረቦችን በፍትሐዊነት ለማሟላት ከፍተኛ ጥረት እያደረገ መሆኑን አስታውቀዋል።
መንግሥት የአካባቢው ዋና ዋና ችግሮች የሆኑትን የመሠረተ ልማት እና የውኃ እጥረቶችን ለይቶ ትኩረት በመስጠት ሌት ተቀን እየሠራ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አብራርተዋል።
ከ2 እና 3 ዓመታት በፊት የነበረውን "ሕዝባችን ተጠምቷል፣ ከብቶቻችን እያለቁ ነው" የሚለውን አሳዛኝ ታሪክ ለመቀየር በተከናወኑ ጠንካራ ሥራዎች፣ አሁን ላይ የቦረና ሕዝብ ስለ ውኃ ችግር ማውራቱን ማቆሙን ጠቁመዋል።
በአሁኑ ወቅት እየተሠራ ያለው ግዙፍ የውኃ ፕሮጀክት ከአንድ እስከ ሁለት ዓመታት ባለው ጊዜ ውስጥ ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅ፣ ሕዝቡ ሰፊ መሬቱን አልምቶ ራሱን ከመመገብ ባለፈ አጎራባች ሀገራትን ጭምር ውኃ የሚያጠጣበት ደረጃ ላይ እንደሚደርስ አረጋግጠዋል።
በዚህም ቦረና የውኃ እጥረት የሚነሳበት አካባቢ ሳይሆን ለጎረቤት ሀገራት ጭምር የንግድ እና የኢኮኖሚ ማዕከል እንደሚሆን ያላቸውን ሙሉ እምነት ገልጸዋል።
ይህም "ገዳ የጥጋብ እና የልምላሜ ዘመን ነው" የሚለው አባባል ከቃላት መፈክርነት ባለፈ በተግባር ተተርጉሞ መሬቱ እንዲለማ እና ሕዝቡ ጠግቦ እንዲኖር መንግሥት የገባውን ቃል ለመፈጸም ሌት ተቀን እየሠራ መሆኑን አስገንዝበዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመጨረሻም ሕዝቡ በልዩነቶች እና በተለያዩ ስሞች ከመከፋፈል ይልቅ ሀገራዊ እና ሕዝባዊ አንድነቱን አጥብቆ እንዲይዝ አሳስበዋል።
ምንም እንኳ የተለያዩ ከፋፋይ ድርጊቶች ቢኖሩም፣ ሕዝቡ አንድነቱን ጠብቆ እና የጋራ ማንነቱን በማስቀደም ለቀጣይ የልማት እና የብልጽግና ምዕራፍ በጋራ መቆም እንዳለበት ጥሪያቸውን አቅርበዋል።
በለሚ ታደሰ