Search

የአዲስ አበባ ወንዞች አዲስ የታሪክ ምዕራፍ

ረቡዕ ግንቦት 26, 2018 148

ከባሕር ጠለል በላይ 2 ሺህ ሜትር ከፍታ ላይ የምትገኘው አዲስ አበባ በርካታ ወንዞች የሚፈስሱባት ብትሆንም በተለያዩ ምክንያቶች ሥነ-ምኅዳሯ በእጅጉ ተጎድቶ ቆይቷል።

በተለይም ፈጣን የከተማ መስፋፋትን ተከትሎ የሕዝብ ቁጥር መጨመሩ የከተማዋ ወንዞች የቆሻሻ መጣያ እና የፍሳሽ ማስወገጃ እንዲሆኑ አድርጓቸው ነበር።

ይህንን የቆየ የሥነ-ምኅዳር እና የጤና ፈተና ለመቀልበስ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (/) አነሳሽነት የተጀመረው የወንዝ ዳርቻ ልማት ፕሮጀክት ግን ለከተማዋ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ከፍቷል።

ይህ ግዙፍ ፕሮጀክት ከእንጦጦ ተራራ ተነሥቶ እስከ አቃቂ የፍሳሽ ማጣሪያ ጣቢያ ድረስ የሚዘልቀውን 56 ኪሎ ሜትር የወንዝ ዳርቻ የማጽዳት፣ የማልማት እና ለአረንጓዴ የሕዝብ መዝናኛነት የማዘጋጀት ዓላማን አንግቦ የተነሣ ነው።

የዚህ ራዕይ አካል የሆነው እና በጠቅላይ ሚኒስትሩ ተመርቆ ለሕዝብ ክፍት የተደረገው የእንጦጦ-ቀጨኔ የወንዝ ዳርቻ ልማት ደግሞ ይህንን ለውጥ በተጨባጭ የሚያሳይ ነው።

ፕሮጀክቱ በከተማዋ ለሚገኙ በርካታ ወንዞች መነሻ እንዲሁም የከተማዋ ሳምባ ከሆነው የእንጦጦ ደን ጋር የተሣሠረ ነው።

በልማቱ አካባቢው ወደ ተፈጥሯዊ ይዘቱ ተመልሶ ለሕዝብ መዝናኛነት እና ለሀገር በቀል ዕውቀቶች ማዕከልነት ክፍት ሆኗል።

ለሁሉም የኅብረተሰብ ክፍሎች ምቹ ሆኖ የተገነባው ይህ የቀጨኔ የወንዝ ዳርቻ ልማት 597 ሔክታር መሬት እና 9.6 ኪሎ ሜትር ርዝመት የሚሸፍን ማራኪ መናፈሻ መሆን ችሏል።

የከተማዋ የውበት ራዕይ ፍሬ የሆኑት አስደናቂ ፓርኮች የውበት ድምቀት ከመሆን ባለፈ ከፍተኛ ማኅበራዊ አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ።

1 ሺህ 300 ሔክታር መሬት ላይ ያረፈው እና "የአዲስ አበባ ሳምባ" በመባል የሚታወቀው የእንጦጦ ተፈጥሮ ፓርክ እንዲሁም በቦሌ ክፍለ ከተማ 26 ሔክታር መሬት ላይ የተዘረጋው የፒኮክ ፓርክ ተጠቃሽ ናቸው።

የፒኮክ ፓርክ ብርቅዬ የሆኑትን ጥቁር ጎፈር አንበሶችን እና አዲስ የአዞ ማቆያን አካትቶ የተገነባ እጅግ ውብ ስፍራ ነው።

ቀበና፣ ቀጨኔ፣ ቁርጡሚ፣ ግንፊሌ፣ ቡልቡላ እና ሀርቡ የመሳሰሉት የአዲስ አበባ ወንዞች ከትናንት የቆሻሻ መጠራቀሚያነት እና የወንጀል መፈጸሚያነት ወጥተው ለአዲስ አበባ ንፁህ ትንፋሽ፣ ለነዋሪዎቿ ደግሞ መዝናኛ እየሆኑ ናቸው።

የእነዚህ ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶች ስኬት የጠንካራ ፋይናንስ እና የዲፕሎማሲ ስትራቴጂ ውጤት ነው።

የልማቱ ስኬት በከተማ ውበት ብቻ ሳይሆን በአካታችነቱ እና በማኅበራዊ ፍትሐዊነቱ ጭምር የሚለካ እንደሆነ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (/) ጠቁመዋል።

ፕሮጀክቶቹ የተሠሩት በሀገር ልጆች መሆኑ ደግሞ ሌላው ትልቅ ስኬት ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደገለጹት ከዚህ ቀደም በውጭ ባለሙያዎች ጭምር ተሞክሮ ያልተሳካው ይህን ፕሮጀክት በሀገር ልጆች ማሳካት ታላቅ ውጤት ነው።

የዚህ ፕሮጀክት ሌላው ትሩፋት ደግሞ በሥራው ሂደት በርካታ ምርጥ ባለሙያዎችን ማፍራት መቻሉ ነው። እነዚህ በተግባር የታነጹ ባለሙያዎች ከዚህ በፊት የወንዝ ዳርቻዎቻቸውን ለማልማት ሞክረው ላልተሳካላቸው የአፍሪካ ሀገራት ጭምር የሚተርፉ ናቸው።

በአጠቃላይ ኢትዮጵያ ለነዋሪዎቿ ምቹ የሆኑ ዘመናዊ እና ብሩህ ከተሞችን የመገንባት ጉዞዋን በጽናት ትቀጥላለች።

 በለሚ ታደሰ