በለንደን በተካሄደው የኢትዮጵያ–ብሪታንያ የወዳጅነት መስተንግዶ ላይ ዲፕሎማቶች፣ የፓርላማ አባላት፣ ባለሀብቶችና ዲያስፖራዎችን ጨምሮ ከ150 በላይ እንግዶች ተሳትፈዋል።
በለንደን የኢትዮጵያ ኤምባሲ ከዌስትሚኒስተር አፍሪካ ቢዝነስ ማህበር (WABA) ጋር በመተባበር ባዘጋጀው በዚህ መድረክ፣ ተሳታፊዎች የኢትዮጵያን ባህላዊ ምግቦች፣ የባህል ትርኢትና የቡና ሥነ-ሥርዓት የተከታተሉ ሲሆን፣ ዝግጅቱ ታሪካዊ የወዳጅነት ግንኙነቱን ይበልጥ ለማጠናከር ከፍተኛ አስተዋፅኦ አበርክቷል።
በብሪታንያ የኢትዮጵያ አምባሳደር አቶ ብሩክ መኮንን፣ በሀገራቱ መካከል ያለው የንግድ፣ የኢንቨስትመንት፣ የትምህርትና የልማት ትብብር በተግባር ማደጉን ገልጸዋል።
አምባሳደሩ የሰው ልጅ መገኛ የሆነችው ኢትዮጵያ የምታካሂዳቸው ሁለንተናዊ የኢኮኖሚ ሪፎርሞች ለውጭ መዋዕለ-ነዋይ ምቹ ሁኔታ መፍጠራቸውን አብራርተዋል።
እንዲሁም በአፍሪካ ትልቁ የአቪዬሽን ማዕከል እንዲሆን የታቀደውን አዲሱን የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ፕሮጀክትን ጨምሮ፣ የኢትዮጵያ ተከታታይ የኢኮኖሚ ዕድገት፣ የዲጂታል ሽግግርና የኢንዱስትሪ ልማት ለባለሀብቶች አዳዲስ የንግድ አማራጮችን ይዘው መቅረባቸውን በሰፊው ጠቁመዋል።
የብሪታንያ የአፍሪካ ተጠባባቂ የንግድ ኮሚሽነር ቤን አይንሴሊ በበኩላቸው፣ ብሪታንያ ኢትዮጵያ ወደ ዓለም አቀፍ የንግድ ሥርዓት ለመቀላቀል የምታደርገውን ጥረት እንደምትደግፍ አረጋግጠው፣ እንደ ቢሾፍቱ አውሮፕላን ማረፊያ ያሉ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን አድንቀዋል።
ኢትዮጵያ ለልማት ሰፊ አቅም እንዳላትና በአፍሪካ ገበያ መሰማራት ለሚፈልጉ የብሪታንያ ኩባንያዎች ሰፊ ዕድል እንደምትሰጥም ገልጸዋል።
ኤምባሲው ለዝግጅቱ መሳካት አስተዋፅኦ ላበረከቱት የዌስት ሚኒስተር ማህበር፣ ቢፋ፣ ቱፋይል ግሩፕና ዳንኪራ የባህል ቡድን ምስጋና ያቀረበ ሲሆን፣ ይህ መርሃ ግብር በቀጣይ ከሰኔ 11 እስከ 12 ቀን 2018 ዓ.ም በብሪታንያ ለሚካሄደው የንግድና ኢንቨስትመንት ፎረም ትልቅ ማስተዋወቂያ ሆኖ አገልግሏል።