ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር) "ኢትዮጵያዊ ዴሞክራሲ ፍለጋ" በተሰኘው መጽሀፋቸው ውስጥ የገዳ ሥርዓትን አስመልክተው ባሰፈሩት ፅሁፍ የገዳ ሥርዓት በጊዜ ልኬት ውስጥ የማይደበዝዝ እና እስከ ዛሬ ድረስ በርካታ ሀገራት ሊያሳኩ ያልቻሏቸው አስገራሚ ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግሮች የሚታዩበት ሥርዓት ነው ብለዋል።
የገዳ ሥርዓት በአፍሪካ እና በኢትዮጵያ ውስጥ ባይወሰን ኖሮ፣ በጣም ብዙ ጸሐፊዎችና ተመራማሪዎች የሚመራመሩበት እና ልምዱን ለዓለም የሚሸጡበት ይሆን እንደ ነበር ያላቸውን እምነት ዶ/ር ተስፋዬ በመጽሃፋቸው ውስጥ በስፋት አትተዋል።
ዶ/ር ተስፋዬ የገዳ ሥርዓትን አስመልክቶ በመጽሀፋቸው ምእራፍ ዐሥራ ሁለት
"የገዳ ሥርዓትና ዴሞክራሲ" በሚል ርእስ ከገጽ 142 ጀምሮ ካስቀመጡት ሀሳብ በጥቂቱ እናጋራችሁ፦
ገዳ ማለት ፕሮፌሰር መሐመድ ሐሰን እንደሚገልፁት "በቋንቋው ተናጋሪ ዘንድ ገዳ የሚለው ቃል ሰፊ የሆነና የጠነከረ ትርጓሜ አለው። የመጀመሪያው ገዳ ማለት ከለላ ወይም ጥላ የሚለውን አገላለጽ የሚወክል ነው ይላሉ፡፡ ከለላ ወይም ጥላ በሚባለው ቃል ውስጥ ደግሞ ሦስት ዓይነት ትርጉም እንዳለው አትተዋል፡፡
የመጀመሪያው መጠለያ (Shelter) የሚለው ትርጉም ያለው ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ መሸሸጊያ (ራስን ለማዳንና ለመጠበቅ የምንገኝበት ሥፍራ) የሚል አለው፡፡ በሦስተኛ ደረጃ ደግሞ ጥላ በኦሮሞ አገላለጽ Guddisa የሚባለውን ትርጉም እንደሚይዝ ይገልጽሉናል፡፡
ከዚህ ትርጉም ውስጥ በተለይም ሦስተኛው ትርጉም ከለላ ወይም ጥላ የሚለው ቃል በኦሮሞ ዘንድ ልዩ ስፍራ የሚሰጠውን ‘ኦዳ’ን የሚወክል ነው፡፡ ምክንያቱም ይህ ትልቁ ዛፍ ‘ኦዳ’ ኦሮሞ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ቁጭ ብሎ ሰብሰብ ብሎ የሚመክርበት የሚሰበስበው እና አቅፎ የሚይዘው ማኅበራዊ ጥላው ነው ማለት ይቻላል፡፡
ኦዳ በጠቅላላ የኦሮሞ አንድነት ምልክት ተደርጎ የሚወሰድ ነው፡፡ ገዳ ልክ እንደ ጥላ ከለላነቱ ሁሉ ኦሮሞ ሁለንተናዊ እንቅስቃሴውን መልክ የሚያሲዝበት እና የሚቃኝነበት ፍልስፍና ጭምር ነው፡፡
በዋርካ ሥር መሰባሰብና የሽምግልና ዳኝነት መስጠት አፍሪካዊ ባህል ነው፡፡
በኢትዮጵያም ከሰሜን እስከ ደቡብ ባሉት ባህሎች ዋርካ ሦስት ባህላዊ ጥቅም ይሰጣል፡፡ የሽማግሌዎች መሰብሰቢያና መፍረጃ፣ የሕዝቡ ማኅበራዊ ኩነት ማከናወኛ እና አልፎ አልፎ ከእምነት ጋር የሚከናወኑ ሥነ ሥርዓቶችና ማካሄጃ ነው፡፡
በዚህ የተነሣ ዋርካ መቁረጥ በብዙ ባህሎች ክልክል ነው፡፡ አንድ ዋርካ በልዩ ልዩ ምክንያት ድንገት ከወደቀም የክፉ ነገር ምልክት ተደርጎ ይታያል፡፡
ፕሮፌሰር መሐመድ ሐሰን ገዳ ጊዜን ለመግለጽ ያገለግላል ይላሉ፡፡ Gaafa Gadaa kami? (በየትኛው ገዳ?)፣ ባለ ሥልጣን ሲሆን ደግሞ Inni Gadaa (እሱ ገዳ ነው)፣ እንዲሁም ሌሎች አገላለጾችን ማለትም Gadaa nagayaa (የሰላም ገዳ)፣ Gadaa quufaa (የጥጋብ ገዳ)፣ Gadaa lolaa (የጦር ገዳ) ወዘተ. ለማለት ይጠቀምበታል ሲሉ ያብራራሉ፡፡
በኦሮሞ የገዳ ሥርዓት ዙሪያ ጥናት ሲያደርግ የቆዩት ተመራማሪ፣ ፕሮፌሰር አስመሮም ለገሠ ፣ ገዳን እንዲህ በማለት ይገልጻሉ፡-
"ገዳ የዕድሜ መዋቅር ሆኖ በየስምንት ዓመት የሚቀባበሉት ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ወታደራዊ እና ፖለቲካዊ ዓላማ ያለው ተቋም ነው። እንደ አንትሮፖሎጂስቶች አገላለጽ በዕድሜ ላይ የተመሠረተ ትልቅ ዕድገት እና ከፍተኛ ሕዝባዊ መዋቅር የሚታይበት ሥርዓት ነው፡፡
ፕሮፌሰር አሥመሮም የገዳ ሥርዓትን የሚተረጉሙት በየስምንት ዓመቱ ከሚካሄደው የሥልጣን ሽግግር ጋር አያይዘው ነው፡፡ በእኔ እምነት ይህ ዕይታና ትንታኔ ተገቢ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡
ምክንያቱም እንኳን ከብዙ ሺህ ዓመታት በፊት ቀርቶ ዛሬ ድረስ፣ በፖለቲካው ዓለም በጣም ፈታኝ ከሚባሉ ነገሮች ውስጥ አንዱ ሥልጣንን በሰላማዊ መንገድ የመያዝና የመልቀቅ ሂደት ነው፡፡ በአፍሪካ አጠቃላይና በኢትዮጵያ በተለይ ደግሞ ዋና ችግር ሆኖ የቆየው ሥልጣንን በአፈ ሙዝ የበላይነት የመቆጣጠር አባዜ ነው፡፡
በዚሁ መነጽር ሲታይ የገዳ ሥርዓት ዴሞክራሲያዊ ልምምዶች ለኢትዮጵያ ብቻም ሳይሆን ለአፍሪካም የሚተርፉ መሆን ይችላሉ፡፡