Search

የ18 ዓመቱ ሞሮኳዊ - አዲሱ የዓለም ዋንጫ ክስተት

እሑድ ሰኔ 07, 2018 84

ዓለም ዋንጫ የትላንት ትዝታ፤ የዛሬ ደግሞ እውነት ነው። በዚህ ግዙፍ የእግር ኳስ መድረክ እልፎች ብደርስበት ብለው ያኖሩት ህልም አለ።

ከነዚህ ህልሞች ውስጥ አንዱ ወደ 2018 ሩሲያ ዓለም ዋንጫ ይወስደናል። የያኔው 10 ዓመት ታዳጊ በስታዲየም ተገኝቶ እግር ኳስን የሚከታተል ደጋፊ ነበር።

ትላንት የወቅቱ የአፍሪካ እግር ኳስ የስበት ማዕከል ሞሮኮ የስፖርቱን ባለ ግዙፍ ታሪክ ብራዚልን ስትገጥም፤ የያኔው ህፃን ኒው ጀርሲ ላይ ወጣት ሆኖ ተገለጠ። ደጋፊ ሳይሆን የተዋጣለት እግር ኳሰኛ ሆኖ መጣ።

ይህ ለእነዛ ባለ ግርማ ሞገስ ተጫዋቾች፣ ለዓለም እግር ኳስ የውጤት ባለ ሟሎች ሊሰጥ ያለን ትኩረት ወደ እርሱ እንዲዘነበል ያደረገ ታዳጊ ማነው? የሚል ጥያቄ ተከተለ።

አሁን አዩብ ቡአዲ የሚለው ስም ገሀድ ወጥቷል። በኒው ጀርሲው ጨዋታ የአማካይ ስፍራ ላይ በተሟላ ተሰጥኦ የታየው ወጣት ማነጋገሩን ቀጥሏል።

ዕድሜው ገና ቢሆንም ቡድን በመምራት ስብዕና፣ የጨዋታውን የፍሰት ሚዛን በመጠበቅ ቡድኑ ከጨዋታ እንዳይወጣ በማስቻል፤ ብሎም ለቡድን አጋሮቹ የሚያቀርባቸው ኳሶች ልክነት እና ጥራት ከወዲሁ አድናቆት እንዲጎርፍለት እያደረገ ነው።

ለፈረንሳዩ ሊል የሚጫወተው ቡአዲ ከዚህ ቀደም በተለያዩ የዕድሜ እርከኖች ለፈረንሳይ የታዳጊ ብሔራዊ ቡድኖችን በአምበልነት እስከመምራት የደረሰ ተሳትፎ ነበረው።

ሆኖም 2026 ዓለም ዋንጫ ሊጀምር ጥቂት ወራት ሲቀሩ፤ ከፈረንሳይ ይልቅ የዘር ሀረጉ ለሚመዘዝባት የአትላስ አናብስቶች ምድር ሞሮኮ መጫወትን መረጠ። ይህ ውሳኔው ደግሞ ቁጭት የሚያስከትል እንዳልሆነ በአሜሪካ ምድሩ ዓለም ዋንጫ መረጋገጥ ጀምሯል።

በምድብ ሦስቱ ሞሮኮ ብራዚልን በገጠመችበት ጨዋታ፤ የሞሮኮ አማካይ ክፍል ልምድን ከተሰጥኦ ባጣመሩት 'ሴልሳኦዎ' እንዳይፍረከረክ አዩብ ቡአዲ የማይተካ ሚና ተጫውቷል።

በጠባብ መስመሮች እና በጫና ውስጥ ሆኖ የሚያደርጋቸው ስኬታማ የኳስ ቅብብሎች፣ ችኩልነት የማይስተዋልበት እንቅስቃሴው እና ከራስ መተማመኑ ጋር ሜዳው ላይ ያሳየው ታታሪነት፤ ባለ ዘንፋላው ፀጉር በዘንድሮው ዓለም ዋንጫ ክስተት ሊሆኑ ይችላሉ ከተባሉ ተጫዋቾች ተርታ እንዲመደብ፤ በቀጣይ ጨዋታዎችስ ምን ሊያስመለክት ይችላል? የሚለውም ተናፋቂ እንዲሆን አድርጓል።

ዓለም ዋንጫ ላይ መጥተው አንዳንዶች አልፎ ሂያጅ፣ ጥቂት ያልሆኑትም የዘመናት ኮከብ ይሆናሉ። ምንአልባት ነገ በፈረንሳይ ምድር ውልደቱ የሆነው አዩብ ቡአዲ ታላቅ እግር ኳሰኛ ከሆነ፤ ያችን የኒው ጀርሲ ምሽት እርሱም እግር ኳስም ሲያስታውሷት ይኖራሉ።

በብሌን ደምበሎ