Search

የነገው ብርሃን እና የሕይወት ስጦታ፤ ከደም ጠብታ እስከ ዐይን ብሌን ልገሳ

እሑድ ሰኔ 07, 2018 60

የአንድ ሰው በጎ ፈቃደኝነት የብዙዎችን የህልውና መስመር የመቀጠል አቅም አለው።

ዘንድሮ አንድ ጠብታ ደም በመስጠት ሕይወትን እናድን በሚል መሪ ቃል የሚታሰበው የዓለም የለጋሾች ቀን፣ ለሌሎች ተስፋ ሲሉ ደም፣ የዐይን ብሌን እና ቲሹን በፈቃደኝነት ለሚለግሱ ወገኖች እውቅና የሚሰጥበት ልዩ ቀን ነው።

አንድ በጎ ፈቃደኛ በአንድ ጊዜ የደም ልገሳ ብቻ እስከ ሦስት የሚደርሱ ሰዎችን ከሞት መታደግ የሚችል ሲሆን፣ ከተለገሰው ደም የሚቀነባበሩት ፕላዝማ፣ ፕሌትሌት እና ቀይ የደም ሴሎች በወሊድ፣ በአደጋ እና በተለያዩ ሕመሞች ለተጎዱ ወገኞች ዋነኛ የሕክምና አማራጭ ይሆናሉ።

ይህ የሕይወት አድን ታሪክ .. 1818 እንግሊዛዊው ሐኪም ጄምስ ብሉንዴል ለመጀመሪያ ጊዜ ከሰው ወደ ሰው ደም በማስተላለፍ አንዲትን እናት ከወሊድ ደም መፍሰስ ከታደገበት ጊዜ ይጀምራል።

በሀገራችን ደግሞ ከሁለተኛው የጣልያን ወረራ ጋር ተያይዞ ለተጎዱ ዜጎች አስቸኳይ እርዳታ ለመስጠት የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ሐምሌ 1 ቀን 1927 .. ተመሠረተ።

በመቀጠልም የደም ባንክ አገልግሎት 1962 .. በዚሁ ማኅበር በይፋ ተጀምሮ፣ ደም ለመሰብሰብና ለማከማቸት መንገድ በመክፈት ወደ ማዕከላዊ የመንግሥት መርሃ ግብር የተሸጋገረ የሕይወት ተስፋ ሆኗል።

ከደም ልገሳ ባለፈ፣ የዐይን ብሌን ልገሳ የዐይን ብርሃን ለሌላቸው ወገኖች ብርሃን የሚመልስ ታላቅ ሰብዓዊ ተግባር ነው። በኢትዮጵያ በየዓመቱ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች በብሌን መጎዳት ምክንያት የማየት ችግር ቢያጋጥማቸውም፣ አሁን ላይ አበረታች ለውጦች እየታዩ ነው።

የኢትዮጵያ የደምና ቲሹ ባንክ አገልግሎት ሥራዎቹን በማስፋፋት የመቶዎችን ብርሃን መመለስ የቻለ ሲሆን፣ በያዝነው በጀት ዓመት ብቻ 350 የዐይን ብሌኖች ተሰብስበው ለታካሚዎች ተላልፈዋል።

በተጨማሪም 500 በላይ ዜጎች ከሕይወት ማለፍ በኋላ ዐይናቸውን ለመለገስ ቃል የገቡ ሲሆን፣ በቅርቡ በጅማ ዩኒቨርሲቲ ሜዲካል ሴንተር የሀገራችን ሁለተኛው የዓይን ባንክ መከፈቱ ተጨማሪ አዲስ ተስፋ ፈጥሯል።

ለጋሽነት የምንሰጠው ነገር ብቻ ሳይሆን የምንተወው ተስፋ በመሆኑ፣ ይህንን በጎ ተግባር ልናጠናክረው ይገባል።

በልዩ እሸቱ