የገዳ ሥርዓት ለኦሮሞ ሕዝብ አንድነት ዋነኛ መሠረት መሆኑን እና እሴቶቹ ይበልጥ ሊጠናከሩ እንደሚገባ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ አሳስበዋል።
"ይህ ሥርዓት ተራ ቅርስ ብቻ ሳይሆን የኦሮሞ ሕዝብ የማንነት፣ የጥንካሬ እና የዕድገት ማዕቀፍ ነው" ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ የዛሬውን ሕያው ማኅበራዊ ሕይወትና የሕዝቡን የወደፊት ዕጣ ፈንታ የሚቀርጽ በመሆኑ ይበልጥ እንዲበለጽግ ክልሉ በትኩረት እየሠራ መሆኑን አብራርተዋል።
በሸገር ከተማ ዳካ ኮራ ‘አርዳ ጂላ’ 71ኛው የቱለማ ኦሮሞ ገዳ የሥልጣን ርክክብ በደማቅ ታሪካዊ ትዕይንት ተካሂዷል። በየስምንት ዓመቱ በሚከናወነው በዚህ ታሪካዊና ባህላዊ የሥልጣን ሽግግር (አላንጌ) ደንብ መሠረት፣ የሜልባ አባ ገዳ የሆኑት ጎበና ሆላ የሥልጣን ዘመናቸውን በማጠናቀቅ ለሙደና አባ ገዳ ጌቱ ተሊላ የሥልጣን በትራቸውን በክብር አስረክበዋል።
የኦሮሚያ ክልል መንግሥት ባከናወነው የባህል ሕዳሴ፣ ተረስተው የነበሩ ጥንታዊ ባህሎችና እሴቶች ዳግም እንዲያንሰራሩ ሰፊ ጥረት አድርጓል። ይህንኑ መሠረት በማድረግም ከታችኛው የትምህርት እርከን ጀምሮ ትውልዱ በገዳ ሥርዓት እሴቶች እንዲታነጽ፣ ሥርዓቱ በሥርዓተ ትምህርት ውስጥ ተካቶ እየተሰጠ ይገኛል።
ጥንታዊ ዕውቀትን ማስቀጠል፣ ታሪካዊ ትረካዎችን ማስተካከል እንዲሁም እሴቶቹን ለኢኮኖሚ ዕድገት፣ ለኪነ ጥበብ፣ ለሚዲያና ለእውቀት ምንጭነት ማዋል የክልሉ መንግሥት ቀዳሚ የትኩረት አቅጣጫዎች መሆናቸውንም ፕሬዚዳንቱ አክለዋል።
የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ጀሚላ ሲምቢሩ በበኩላቸው፣ የኦሮሞን ታሪክ፣ ባህልና ሥነ ምግባር ለማሳደግ በመሠራት ላይ ያሉትን ተቋማዊ ሥራዎች አብራርተዋል። ቢሮው ባለፉት ዓመታት የ‘አርዳ ጂላ’ (የባህልና ሥርዓት ማከናወኛ) ቦታዎችን ከማልማት ባለፈ፣ በገዳ ሥርዓት ላይ ያተኮሩ የጥናትና ምርምር ሥራዎችን ሲያከናውን መቆየቱን አስታውሰዋል።
በቀጣይም አላንጌውን ከተረከበው አዲሱ የቱለማ ገዳ አመራር ጋር በመሆን የ‘አርዳ ጂላ’ ቦታዎችን ማልማትን ጨምሮ ለሥርዓቱ ዕድገት የሚበጁ ተጨማሪ የልማት ሥራዎች እንደሚሠሩ አረጋግጠዋል።
ከቀናት በፊት ጀምሮ በስፍራው የተሰባሰቡ አባ ገዳዎችና የተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች በርካታ ባህላዊና ሃይማኖታዊ ሥርዓቶችን ሲያከናውኑ ሰንብተዋል። የሰው ልጅንና የተፈጥሮን መብት የሚያጸኑ ሕጎችም በአባ ገዳዎቹ ታውጀዋል።
በዕለቱ የሥልጣን ሽግግር ሥነ ሥርዓት ላይ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳን ጨምሮ፣ የጨፌ ኦሮሚያ አፈ ጉባኤ ወ/ሮ ሳዳ አብዱራህማን፣ የሸገር ከተማ ከፍተኛ አመራሮች፣ አባ ገዳዎች፣ ሀደ ሲንቄዎች እና በርካታ የአካባቢው ነዋሪዎች ታድመዋል።