የሰው ልጅ ሥልጣኔን፣ ፍልስፍናንና የፖለቲካ ሥርዓትን ከምዕራባውያን ማዕድ ብቻ ለመቅሰም በሚማስንበት በዚህ ዘመን፣ ጥቁር አፍሪካውያን ከዘመናት በፊት የገነቡትና ለዓለም አቀፍ ዲሞክራሲ ማሳያ የሚሆን አንድ ድንቅ የጥበብ ማከማቻ በኢትዮጵያ ምድር ይገኛል። እርሱም በዩኔስኮ የማይዳሰሱ የዓለም ቅርሶች ዝርዝር ውስጥ የተመዘገበውና በኩራት የሚጠራው የኦሮሞ ገዳ ሥርዓት ነው።
ይህ ሥርዓት የኦሮሞ ሕዝብ ማንነት ነጸብራቅ ብቻ ሳይሆን ፍትሐዊ የፖለቲካ አስተዳደር፣ ሰላም፣ አብሮነትና ወንድማማችነት በጥልቀት የተሳሰሩበት፣ ኢትዮጵያ ለዓለም ያበረከተችው ድንቅና ሕያው ፍልስፍና ነው።
ዛሬ በተከናወነው የ71ኛው የገዳ ቱለማ የሥልጣን ሽግግር ሥነ-ሥርዓት፣ ዛሬም ድረስ ሥርዓቱ ምን ያህል ሕያው፣ ጠንካራና የማይደበዝዝ ማኅበራዊ መዋቅር እንደሆነ ዳግም ለዓለም በተግባር መስክሯል።
የገዳ ሥርዓት መሠረቱ ፍጹም ዲሞክራሲያዊና ፍትሐዊ በሆነ የሕዝብ ውክልና ላይ የተገነባ በመሆኑ የሚደነቅ ነው። ሥልጣን ለአንድ ግለሰብ ወይም ቡድን ለዘላለም የሚሰጥ ርስት ሳይሆን በየስምንት ዓመቱ ለሚተካ አዲስ ትውልድ የሚተላለፍ የተቀደሰ አደራ ነው።
ሥልጣን የሕዝብ ነው፤ መሪው ደግሞ የሕግ ተገዥ ብቻ ነው የሚለው የገዳ መርህ፣ ዛሬ በዓለማችን ላይ ለሚታየው የፖለቲካ ቀውስ ፍጹም መድኃኒት ሊሆን የሚችል ታላቅ እሴት ነው።
በቱለማ ገዳ ሥርዓት የታየው ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር የዚህ እውነት ማሳያ ነው፤ ላለፉት ስምንት ዓመታት በታማኝነትና በስኬት ሕዝባቸውን የመሩት የሜልባው አባ ገዳ ጎበና ሆላ፣ የሥልጣንና የሉዓላዊነት ምልክት የሆነውን አለንጋ ለአዲሱ የሙደናው አባ ገዳ ጌቱ ተሊላ በይፋ አስረክበዋል።
ሥልጣናቸውን ያጠናቀቁት መሪ ወደ ዩባ አማካሪነት ደረጃ በመሸጋገር አዲሱን አመራር በዕውቀትና በምክር ለማገልገል ወደ ኋላ ይቀመጣሉ። ይህ ዓይነቱ ሰላማዊ፣ ክብረ-በዓላዊ እና ፍጹም ቅንነት የተሞላበት የሥልጣን ሽግግር፣ የዘመናዊው ዓለም የፖለቲካ ልሂቃን ሊማሩት የሚገባ ትልቅ የዲሞክራሲ ትምህርት ቤት ነው።
በገዳ ሥርዓት ውስጥ መሪነት በዘፈቀደ፣ በሕዝብ ቁጥር ብልጫ ወይም በገንዘብ ኃይል የሚገኝ ሹመት አይደለም። ለአባ ገዳነትና ለካቢኔ አባልነት የሚመረጡ ዕጩዎች በሕይወት ዘመናቸው የነበራቸውን የሞራል ሥነ-ምግባር፣ የባህል ዕውቀትና የፍትሐዊነት ታሪክ የሚያጠና ጥልቅና ምስጢራዊ ማጣሪያ ይደረግባቸዋል።
ይህን ጥብቅ መመዘኛ አልፈው የተመረጡት አሥራ አምስት ግለሰቦች ከተለያዩ የቱለማ ንዑሳን ጎሳዎች በጥንቃቄ የተውጣጡ ሲሆኑ ከእነሱ መካከል ደግሞ ሳግሊ የተሰኘው የዘጠኝ ሰዎች ምክር ቤት ተመርጧል።
ይህ ምክር ቤት የሥልጣን ክፍፍልን በተግባር የሚያሳይ ሲሆን አባ ሴራ፣ አባ ጨፌ፣ አባ ሳዓ፣ አባ አለንጋ እና አባ ኦላፊ ጋንዳ የተባሉ ቁልፍ የአስተዳደር መዋቅሮችን ያካተተ ነው።
ይህ መዋቅር የሥልጣን ማዕከላዊነትን በማስወገድ፣ እያንዳንዱ የኅብረተሰብ ክፍል በአስተዳደሩ ውስጥ የራሱ ድምፅ፣ መብትና ውክልና እንዲኖረው ያደርጋል።
ገዳ የፖለቲካ ሥርዓት ብቻ አይደለም፤ የማኅበረሰቡን ሰላም፣ ዕርቅና አንድነት የሚያጸና የሕይወት ፍልስፍና እንጂ። ሥርዓቱ በማኅበረሰቡ መካከል የሚነሱ ግጭቶችን በውይይት፣ በካሳ እና በይቅርታ የሚፈታበት የዳበረ ባህላዊ የፍትሕ ሥርዓት አለው። ከዚህም በተጨማሪ የሴቶችን መብትና ክብር ለመጠበቅ፣ ለተፈጥሮና ለፈጣሪ ጥልቅ አክብሮት ለመስጠት የሚያስችሉ የሞራል ሕጎች የተደነገጉበት ማዕቀፍ ነው።
በቅርቡ የኦሮሚያ ጨፌ አፈ-ጉባኤ ወይዘሮ ሳዓዳ አብዱራህማን እንደገለጹት፣ ገዳ የትናንትና የዛሬ ብሔራዊ ማንነታችን ምስጢር ነው፤ ሕዝባችን ከውጭ የመጣበትን ወረራና ሽብርተኝነት እየመከተ ማንነቱን ጠብቆ እንዲኖር ያደረገ ታላቅ ጋሻ ነው። ይህ የሚያሳየው ገዳ ለአንድነትና ለሀገር ግንባታ ያለውን የማይተካ ሚና ነው።
በታሪካዊውና ጥንታዊው የደካ ቆራ፣ ኦዳ ናቤ እና ጨፌ ዶንጎራ ስፍራዎች ላይ የተከናወኑት እነዚህ የገዳ ሥነ-ሥርዓቶች፣ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ምን ያህል ጥልቅና የበለጸገ የማኅበራዊ ስምምነት ታሪክ እንዳላቸው ማረጋገጫዎች ናቸው።
የገዳ ሥርዓት የኦሮሞ ሕዝብ ለኢትዮጵያ፣ ኢትዮጵያ ደግሞ ለዓለም ያበረከተችው ድንቅ የዲሞክራሲና የሰላም ስጦታ ነው። ዛሬ የዚህን ሥርዓት እሴቶች ለማጠናከርና ታሪካዊ ቦታዎችን ለማልማት የሚደረገው ጥረት፣ ትውልዱ ባህሉን አውቆ ነፃነቱንና አንድነቱን እንዲጠብቅ ትልቅ መሠረት ይጥላል።
ገዳ ትናንትን ዛሬ ላይ አገናኝቶ ወደ ነገ የሚያሻግር፣ ዘመናትን የተሻገረ የጥቁር ሕዝቦች የዲሞክራሲ ማማ ነው!
በበረከት ሽመልስ