ገዳይ የሆነውን የወባ ትንሽ መራባት በ26 በመቶ መቀነስ እንደሚችል የተነገረለትን አዲስ መፍትሄ ዋና ቢሮውን በስፔን ያደረገው (ISGlobal) የተሰኘ የተመራማሪዎች ቡድን ይፋ አድርጓል።
ይህ በክኒን መልክ የተዘጋጀው መድኃኒት የወባ በሽታ ስርጭት በሚበዛበት ወቅት በወር አንድ ጊዜ የሚወሰድ መሆኑ ተገልጿል።
ይህን ክኒን የወሰደውን ሰው በመንደፍ ደሙን የመጠጠች የወባ ትንሽ ከ24 እስከ 48 ሰዓታት ባለው ጊዜ ውስጥ ተመርዛ እንደምትሞት በጥናቱ ማረጋገጣቸውን የሕክምና ተመራማሪዎቹ አሳውቀዋል።
በየዓመቱ በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ሰወች በወባ በሽታ ምክንያት በሚሞቱባት አፍሪካ መሞከሩም ተገልጿል።
የወባ ስርጭቱ ከፍተኛ በሆነባቸው ሞዛምቢክ እና ኬንያ ውስጥ በሚገኙ 20 ሺህ ሰዎች ላይ በተደረገው ጥናት አዲሱ መድኃኒት የወባ በሽታ ስርጭትን በ26 በመቶ መቀነስ እንደቻለ ነው የተነገረው።
የምርምር ውጤቱ በዓለም ላይ ገዳይ ከሆኑ በሽታዎች መካከል ዋናኛ የሆነውነ የወባ በሽታ ስርጭትን በእጅጉ እንደሚቀንስ እና ምናልባትም ከዓመታት በኋላ በስታውን ለማጥፋት ታላቅ መፍትሄ ሊሆን እንደሚችል ተስፋ ተጥሎበታል።
ለዓመታት ምርምር ሲካሄድበት የቆየው ይሄው ውጤት የተሳካ እንደሆነ መገለጹን የሕክምና ግኝቶችን በመዘገብ የሚታወቀው ሳይንስ ቴክ ዴይሊ አስነብቧል።
በዓለም ላይ በየዓመቱ በወባ በሽታ ከሚሞቱ ሰወች 95 በመቶ የሚሆኑት በአፍሪካ የሚገኙ ሲሆን፤ እ.አ.አ. በ2023 በተሰራው ጥናት መሰረት 569 ሺህ አፍሪካውያን በወባ በሽታ የተነሳ ሕይወታቸው አልፏል።