ጥቅምት 12 ቀን 2016 ዓ.ም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) "የዛሬ አምስት ዓመት አዲስ አበባ በአፍሪካ ውስጥ እጅግ ውብ ከሚባሉ ከተሞች አንዷ ትሆናለች" ሲሉ ተናግረው ነበር።
ያኔ ንግግራቸውን ከሰሙት መካከል የመዲናዋን የዛሬ ገጽታ በዐይነ ኅሊናቸው የሣሉት ጥቂቶች ነበሩ።
በወቅቱ ንግግሩ ከተራ የፖለቲካ ተስፋ በላይ ትርጉም አይኖረውም ብለው የተጠራጠሩ ቢኖሩም፣ ዛሬ ግን አዲስ አበባ በአጭር ጊዜ ውስጥ እጅግ ማራኪ፣ ጽዱ እና ዘመናዊ ዲፕሎማሲያዊ ማዕከል በመሆን ራዕዩን በተግባር አሳይታለች።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመዲናዋ ተበታትነው የሚገኙትን እምቅ አቅሞች ወይም "ያልተያያዙ ትላልቅ ዶቶችን" በማገናኘት ከተማዋን በአዲስ መልክ የመገንባት ዕቅድ እንዳላቸው አስረድተውም ነበር።
ይህ አርቆ አሳቢ የከተማ ልማት ፍልስፍና ታሪካዊ ክስተቶችን የሚያስታውስ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳስታወሱት፣ ንጉሥ ላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናትን መገንባት በጀመሩበት ወቅት "ድንጋይ መቆርቆር የስንፍና ምልክት ነው" በማለት ያሾፉባቸው ነበሩ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፈጣሪዎች እና አልሚዎች ሁልጊዜም በዘመናቸው ካሉ "አውርቶ አደር" ተቺዎች ጋር መጋፈጣቸው አይቀርም የሚል እሳቤ አላቸው።
ዛሬ በኮሪደር ልማቱ እየታየ ያለውም ይኸው እውነታ ነው፤ "እኛ የምንሠራው ለዛሬ ብቻ ሳይሆን ለነገ እና ለቀጣዩ ትውልድ ነው፤ ነገ የሚፈርስ ዳስ አንሠራም" በሚለው መርሐቸው ለትውልድ የሚሻገር ዘላቂ ሥራ እየተሠራ ይገኛል።
"የመደመር መንግሥት" መጽሐፍ ላይ እንደተብራራው፣ ከተሜነት የብልጽግና መዳረሻ እና የኢኮኖሚ ሞተር ነው።
ከተማን ማዘመን ረጃጅም ሕንፃዎችን ከመገንባት ባለፈ ሰፊ የእግረኛ እና የሳይክል መንገዶችን፣ አረንጓዴ ስፍራዎችን እና ምቹ መሠረተ ልማቶችን ማካተትን ይጠይቃል።
አዲስ አበባ ላይ በተግባር ሥራ ላይ ውሎ አዲስ አበባን ምርጥ የአፍሪካ ከተማ ያደረገው ይኸው ሰዎችን ማዕከል ያደረገው ፍልስፍና ነው።
ከዚህ ቀደም የተገነቡት አንድነት ፓርክ፣ እንጦጦ ፓርክ፣ ወዳጅነት አደባባይ እና የዓድዋ ድል መታሰቢያ የዚህ ዘመናዊ አስተሳሰብ ማሳያዎች ናቸው።
በዚህም የኮሪደር ልማቱ በግንባታው ሂደት ለበርካታ ዜጎች ሰፊ የሥራ ዕድል ከመፍጠሩም በላይ፣ የካርቦን ልቀትን በመቀነስ የነዋሪዎችን ጤና እና ደኅንነት የሚጠብቅ ንፁህ አካባቢን መፍጠር ችሏል።
እነዚህ ስልታዊ ለውጦች አዲስ አበባን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለበርካታ ሽልማቶች አብቅተዋታል።
በ2015 ዓ.ም በናይሮቢ በተካሄደው የአፍሪካ ስማርት ሲቲዎች ኢንቨስትመንት ጉባኤ ላይ 36 የአፍሪካ ከተሞችን በመብለጥ ‘የዓመቱ ምርጥ ስማርት ሲቲ' ሽልማትን አሸንፋለች።
እንዲሁም የተባበሩት መንግሥታት የአፍሪካ አዳራሽ (Historic Africa Hall) እድሳት ፕሮጀክት የሞደርኒዝም ጥበቃ ሽልማትን (World Monuments Fund/Knoll Modernism Prize) ተቀዳጅቷል።
ይህ ሽልማት ከተመሠረተበት እ.ኤ.አ. 2008 ጀምሮ በአፍሪካ አህጉር ሲሰጥ አዲስ አበባ የመጀመሪያዋ ነች።
እነዚህ ስኬቶች ከተማዋ እ.አ.አ በ2027 የዓለም አየር ንብረት ለውጥ ጉባኤን (COP32) እንድታስተናግድ ትልቅ መተማመኛ ፈጥረዋል።
በአዲስ አበባ የተመዘገበው ይህ ስኬታማ የከተማ ማዘመን ልምድ በአሁኑ ወቅት ከ70 በላይ ወደሚሆኑ የሀገራችን ከተሞችም እንዲስፋፋ ተደርጓል።
ይህ አዲስ የከተማ ማሻሻያ ፍልስፍና በቱሪዝም ዘርፉ ላይም ታይቶ የማይታወቅ መነቃቃት ፈጥሯል።
በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያዎቹ ዘጠኝ ወራት ብቻ ከ1.5 ሚሊዮን በላይ ከሚሆኑ የውጭ ቱሪስቶች ከ2.6 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ተገኝቷል።
በተባበሩት መንግሥታት የቱሪዝም ድርጅት (UN Tourism) መረጃ መሰረትም ኢትዮጵያ እ.አ.አ በ2025 የዓለም አቀፍ ቱሪስቶችን ፍሰት በ15 በመቶ በማሳደግ ፈጣን ዕድገት እያስመዘገቡ ካሉ የቱሪዝም መዳረሻዎች ተርታ ተሰልፋለች።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ይህን ግዙፍ ልማት ሲያከናውን ያጋጠሙትን ማኅበራዊ እና ሕጋዊ ተግዳሮቶች ሰብአዊነትን በተላበሰ መንገድ ለመፍታት ያደረገው ጥረት የልማቱን ፍትሐዊነት ያረጋግጣል።
ከተማዋን ለሕፃናት፣ ለወጣቶች እና ለአካል ጉዳተኞች ጭምር ምቹ በማድረግ የቦታ ፍትሐዊነትን ማረጋገጥ ተችሏል።
ጥቅምት 12 ቀን 2016 ዓ.ም የተነገረው ራዕይ ዛሬ እውን ሆኖ፣ አዲስ አበባ በምድረ አፍሪካ ውብ፣ ተመራጭ እና የሁሉንም ነዋሪዎቿን ፍላጎት ያማከለች መዲና መሆኗን በተግባር እያረጋገጠች ትገኛለች።
በዚህ ውስጥ ታዲያ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሚና ከፍተኛ ነው። የከተማ አስተዳደሩ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ኢንሼቲቭ ወደ መሬት በማውረድ መዲናችን ዛሬ ለደረሰችበት ገጽታ ሌት ተቀን በመሥራት ኃላፊነቱን ተወጥቷል።
በአዲስ አበባ የተመዘገበው ይህ ስኬታማ የከተማ ማዘመን ልምድ በአሁኑ ወቅት ከ70 በላይ ወደሚሆኑ የሀገራችን ከተሞችም እንዲስፋፋ ተደርጓል።
በለሚ ታደሰ