Search

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በዓለም ፈጣን ዕድገት ካስመዘገቡ ኢኮኖሚዎች አንዱ ነው - የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት

ቅዳሜ ግንቦት 29, 2018 56

የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ባወጣው መግለጫ፣ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ 2017 በጀት ዓመት 9.2 በመቶ ዕድገት አስመዝግቧል፤ ይህም በዓለም ላይ ፈጣን ዕድገት ካስመዘገቡ ኢኮኖሚዎች አንዱ ያደርገዋል ብሏል።

ያለፉት ዓመታት እውነታ በግልጽ እንደሚያሳየው፣ የመንግሥት ቃል የተስፋ ቃል ብቻ አልነበረም፤ ይልቁንም የተከናወኑት ውጤት ተኮር ተግባራት እና የተመዘገቡት ውጤቶች በተጨባጭ የሚታዩ ናቸው ብሏል።

ይህን መነቃቃት መሠረት በማድረግ የኢኮኖሚ ዕድገቱ 2018 በጀት ዓመት 10.2 በመቶ ይደርሳል ተብሎ ይጠበቃል።

የኢኮኖሚ ዕድገቱ ግብርና፣ ኢንዱስትሪና አገልግሎት ዘርፎችን ያካተተና ሰፊ መሠረት ያለው ሲሆን፣ በሂደት ግን ኢንዱስትሪው የዕድገቱ ዋነኛ አንቀሳቃሽ ኃይል ሆኖ እየወጣ ይገኛል።

ይህም መንግሥት ለማኑፋክቸሪንግ፣ ለኢንዱስትሪ ልማት፣ ለዕሴት ጭመራና ለውጭ ገበያ ተኮር ምርቶች የሰጠውን ቀጣይነት ያለው ትኩረት የሚያሳይ እንደሆነ መግለጫው ያትታል።

እነዚህ ውጤቶች እንዲሁ ግምቶች ብቻ ሳይሆኑ በጠቅላይ ሚኒስትሩ 100 ቀናት የሥራ አፈጻጸም የግምገማ ሥርዓት አማካኝነት ክትትል የሚደረግባቸው የተጠያቂነትና የታቀደ አመራር ፍሬዎች ሲሆኑ፣ በዚህም አጠቃላይ የወጪ ንግድ ገቢ 2016 . ወዲህ 100 በመቶ ገደማ ጭማሪ በማሳየት 20 ቢሊዮን ዶላር ይደርሳል ተብሎ ይጠበቃል።

የዋጋ ግሽበትም ወደ ታች ማሽቆልቆሉን በመቀጠል አሁን ላይ ወደ አንድ አሐዝ ደረጃ እየተቃረበ ይገኛል፤ ይህም በቅርብ ዓመታት ውስጥ በቤተሰቦችና በንግዶች ላይ ከባድ ጫና ፈጥሮ ከነበረው ባለ ሁለት አሐዝ የዋጋ ግሽበት አንጻር ትልቅ መሻሻል ነው።

ይህ ስኬት የተመዘገበው ዓለም አቀፍ የኃይል አቅርቦትና ሌሎች ስትራቴጂያዊ ቁሳቁሶችን ገበያ ያናጋው የመካከለኛው ምስራቅ ወቅታዊ ጂኦፖለቲካዊ ውጥረትን ጨምሮ ውጫዊ ጫናዎች ባሉበት ወቅት ነው።

የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ አጀንዳ ከተጀመረ ወዲህ መንግሥት ከውጭ ምንጮች ምንም ዓይነት አዲስ የንግድ ብድር ስምምነት ያላደረገ ሲሆን፣ ይህም የሀገራችንን የብድር ዕዳ ጫና በከፍተኛ ሁኔታ አቅልሎታል።

ከእነዚህ ቁጥሮች በስተጀርባ ኢትዮጵያውያን በዓይናቸው የሚያዩትና በእጃቸው የሚዳስሱት ተጨባጭ ለውጥ አለ።