Search

የሀገርን ሉዓላዊነት ለማስከበር በተግባር የተፈተነ አመራርነት ወሳኝ ነው፡- ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ

ቅዳሜ ግንቦት 29, 2018 38

መከላከያ ሠራዊቱ በታላቅ ተጋድሎና መስዋዕትነት የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ያስጠበቀ፣ የዳር ድንበሯን ያስከበረና ለሕዝቧ ሰላምና ልማት መረጋገጥ ግዳጅና ተልዕኮዎቹን በብቃት የተወጣ የሕዝብ ኩራት መሆኑን የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ተናገሩ፡፡

የሁርሶ ዕጩ መኮንን ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት 27 ዙር የፅናት ኮርስ ዕጩ መኮንኖችን በዛሬው ዕለት አስመርቋል። የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት ኢትዮጵያ የጀግኖች እና የአርበኞች ሀገር ናት ብለዋል፡፡

ባለፉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ ከውጭ ኃይሎች የገንዘብ ድጋፍና ተልዕኮ በመቀበል ሀገርን ለመበተን ሴራ አንግበው የሚንቀሳቀሱ ኃይሎችን ህልም ማምከን መቻሉንም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ገልጸዋል።

ዕጩ መኮንኖቹ ሕዝብና መንግሥት የጣሉባቸውን አደራ በመቀበል፣ ዘመኑ የሚጠይቀውን የአመራርነት ብቃት በመላበስ፣ በፈተናዎች ውስጥ ፈጣን ውሳኔ በመስጠት፣ በከፍተኛ ሥነ ምግባር፣ በሙያዊ ታማኝነት እንዲሁም በሰብዓዊነትና በሀገር ፍቅር ስሜት ሀገራቸውን በቆራጥነት እንዲያገለግሉ አሳስበዋል።

 

የትምህርት ቤቱ አዛዥ ኮሎኔል ከድር ጫጮ በበኩላቸው፣ ተመራቂዎቹ የውጭ ጠላቶችንና የሀገርን ዕድገት የማይፈልጉ የውስጥ ተላላኪዎችን ሴራ ለማክሸፍ የሚያስችል በቂ ሥልጠና መውሰዳቸውን ገልጸዋል።

ለሰልጣኞቹ የአካል ብቃት፣ የሥነ ልቦና፣ የአመለካከትና የአመራር አቅምን የሚያጎለብቱ ሥልጠናዎች ከመውሰዳቸውም በላይ፣ ወቅታዊውን የሳይበር ደኅንነት ሁኔታ የተገነዘቡና በዘርፉ በቂ ዕውቀት የጨበጡ መሆናቸውንም አብራርተዋል።

ዕጩ መኮንኖቹ በትምህርት ቤቱ በቆዩባቸው ጊዜያት የቀሰሟቸው የፅንሰ ሐሳብና የተግባር ትምህርቶች በቀጣይ የሚሰጣቸውን ኃላፊነት በብቃት ለመወጣት እንደሚያስችላቸው ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ፣ የኢትዮጵያ አየር ኃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ፣ የመከላከያ ትምህርትና ሥልጠና ዋና መምሪያ ኃላፊ ጄኔራል ይመር መኮንን፣ የመከላከያ ሠራዊት የመረጃ ዋና መምሪያ ኃላፊ ጄኔራል ጌታቸው ጉዲና እንዲሁም ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

 

በቴዎድሮስ ታደሰ