Search

ለኢትዮጵያ የምርጫ ሳይሆን የህልውና ጉዳይ የሆነው የባሕር በር ጉዳይ

ቅዳሜ ግንቦት 29, 2018 55

ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት በዓለማችን በሕዝብ ቁጥር ቀዳሚዋ የባሕር በር አልባ አገር ናት። ይሁን እንጂ የባሕር በር ጥያቄ ለአገሪቱ የቅርብ ጊዜ የፖለቲካ ፈጠራ ሳይሆን፤ ከታሪክ፣ ከመልክዓ ምድር፣ ከኢኮኖሚ እና ከብሔራዊ ደኅንነት ጋር በጥብቅ የተሳሰረ መዋቅራዊና የህልውና ጉዳይ ነው።

ኢትዮጵያ በታሪኳ አብዛኛውን ዘመን የባሕር በር ባለቤት ነበረች። በጥንታዊው የአክሱም ሥልጣኔ ዘመን የአዱሊስ ወደብን በመጠቀም የዓለም የንግድና የባህር ኃይል ተዋናይ ነበረች።

20ኛው ክፍለ ዘመንም የምጽዋ እና የአሰብ ወደቦችን ትጠቀም ነበር።

 ይሁን እንጂ ... 1993 የኤርትራን መገንጠል ተከትሎ በአንድ ጀምበር በተጠነሰሰባት ሴራ የባሕር በር አልባ ሆናለች። ይህ ክስተት በሕዝቡ ሥነ-ልቦና ውስጥ እስከ ዛሬ ድረስ እንደ ትልቅ መዋቅራዊ ጠባሳ ይታያል።

በጂኦግራፊ ረገድ አገሪቱ የምትገኝበት የአፍሪካ ቀንድ ለዓለም ፖለቲካና ንግድ እጅግ ስሱ ቦታ ነው። ከዓለም የንግድ ፍሰት 12% የሚስተናገድበት የባብ ኤል-መንደብ ጥቂት ኪሎ ሜትሮች ብቻ እየራቃት፣ ኢትዮጵያ በመሬት መከበቧ ታላቅ መልክዓ ምድራዊ መዛባት እየፈጠረ ይገኛል።

የባሕር በር ማጣት የሚጠይቀው የኢኮኖሚ ዋጋ እጅግ ከፍተኛ ነው። በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ 90% በላይ የወጪና ገቢ ንግዷን የምታካሂደው በጅቡቲ ወደብ በኩል ሲሆን፣ ለዚህም በየዓመቱ በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር የውጭ ምንዛሬ ለወደብ ኪራይ ታወጣለች።

ይህም ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ መሠረታዊ ቁሶች (ማዳበሪያ፣ ነዳጅ፣ መድኃኒት) ዋጋ እንዲንርና የኑሮ ውድነት እንዲባባስ እያደረገ ይገኛል። ከተሞች እየሰፉና የሕዝብ ቁጥር በከፍተኛ ፍጥነት እየጨመረ ባለበት ሁኔታ፣ ግዙፉን የንግድ ፍሰት በነፃነት የሚያስተናግድ የራሷ «የኢኮኖሚ ሳንባ» ያስፈልጋታል የሚለው ሀሳብ ስትራቴጂካዊ በሆነ መልኩ በለውጡ መንግሥት መሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (/) በመነሳቱ፣ ከኢትዮጵያ አልፎ የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ አጀንዳ ወደ መሆን ተሸጋግሯል።

በብሔራዊ ደኅንነት ረገድም የሕዝብ መሠረታዊ አቅርቦት ሙሉ በሙሉ በሌላ ሉዓላዊ አገር መረጋጋትና ፖሊሲ ላይ መመሥረቱ ከፍተኛ ስልታዊ ተጋላጭነት ይፈጥራል።

ቀይ ባህር የልዕለ-ኃያላን የጦር ሰፈር መፎካከሪያ በሆነበት በዚህ ወቅት፣ ኢትዮጵያ የባህር ኃይል መሸሸጊያና የራሷ ይዞታ ሳይኖራት መቅረቱ በቀጣናዊ የኃይል ሚዛን ድርድር ላይ አቅሟን ያዳክመዋል።

 የባህር ላይ ወንበዴነትንና ሕገ-ወጥ ዝውውርን ለመከላከልም የባህር በር ማግኘት የግድ ይላል።

ለኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ የቅንጦት ወይም የፖለቲካ ትርፍ ፍለጋ ሳይሆን የህልውና መሠረት ነው።

 በመሆኑም አገሪቱ አሁን ባለው ዓለም አቀፋዊ ሕግ ማዕቀፍ ውስጥ በመሆን፣ ከጎረቤት አገራት ጋር በጋራ ጥቅምና በዲፕሎማሲያዊ ድርድር፣ «አሸናፊ-አሸናፊ» (Win-Win) መርህን በመከተል የባህር በር ለማግኘት የምታደርገው ጥረት የማይቀለበስ ስልታዊ ግዴታ መሆኑ ታምኖበት እየተሠራ ይገኛል።

ትውልዱም የባሕር በር አጀንዳ መሠረታዊ መሆኑን ተቀብሎ በተከታታይነት የመሥራት ኃላፊነት አለበት።

በመሐመድ ፊጣሞ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: