በሶማሌ ክልል ጎዴ ከተማ በ2.5 ቢሊዮን ዶላር ኢንቨስትመንት የሚገነባው ግዙፍ የማዳበሪያ ፋብሪካ፣ የኢትዮጵያን የግብርና ግብዓት እጥረት በዘላቂነት በመፍታት ሀገራዊ የምግብ ሉዓላዊነትን የሚያረጋግጥ ስትራቴጂካዊ ፕሮጀክት ነው።
ከዳንጎቴ ግሩፕ ጋር በመተባበር የሚገነባውና በ40 ወራት ጊዜ ውስጥ ተጠናቆ ወደ ምርት ይገባል ተብሎ የሚጠበቀው ይህ ፋብሪካ፣ በዓመት እስከ 3 ሚሊዮን ቶን ማዳበሪያ የማምረት አቅም ይኖረዋል።
ኢትዮጵያ ባለፉት የለውጥ ዓመታት በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት እና በሌማት ትሩፋት ኢኒሼቲቮች ያስመዘገበችው አንጸባራቂ ስኬት፣ የሀገሪቱን የግብርና ምርታማነት በከፍተኛ ደረጃ አሳድጎታል።
ይህንን በፍጥነት እያደገ የመጣ የሰብል ልማት አቅም በዘላቂነት ለመደገፍና የአርሶ አደሩን የዘመናት የማዳበሪያ እጥረት ጥያቄ በአስተማማኝ ሁኔታ ለመመለስ የፋብሪካው መገንባት ወሳኝ ሚና ይጫወታል።
በተጨማሪም ፋብሪካው ሀገራችን በየዓመቱ ለማዳበሪያ ግዢ የምታወጣውን በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር የውጭ ምንዛሬ በሀገር ውስጥ ምርት ለመተካት ያስችላል፤ ይህም የተቆጠበውን ሀብት ለሌሎች መሠረታዊ የልማት ስራዎች ለማዋል አቅም ይፈጥራል።
ከሀገር ውስጥ ፍላጎት ማሟላት ባሻገር፣ ምርቱን ለጎረቤት ሀገራት በመላክ ተጨማሪ የውጭ ምንዛሬ የሚያስገኝ አዲስ የኢኮኖሚ አቅም ይፈጥራል።
በአጠቃላይ በጎዴ የሚገነባው ይህ የ3 ሚሊዮን ቶን ማዳበሪያ ፋብሪካ፣ የኢትዮጵያን ግብርና ከተረጂነት አስተሳሰብ ሙሉ በሙሉ አላቆ ወደ አምራችነት እና አህጉራዊ ተወዳዳሪነት የሚያሸጋግር ታሪካዊ ምዕራፍ ነው።
በሃና ምንዳሁን
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: