የእንጅባራ ከተማ በልጇ "በሕዳሴ ዘመኑ" የ12 ዓመታት የልፋት፣ የትጋት እና የጥረት ውጤት ደምቃ ሰንብታለች፡፡
የአገው ምድር 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ያፈራት ተማሪ "ሕዳሴ ዘመኑ" በ2018 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል በተፈጥሮ ሳይንስ ሀገር አቀፍ መልቀቂያ ፈተና 583 ነጥብ በማምጣት በሀገር አቀፍ ደረጃ በተፈጥሮ ሳይንስ 2ኛ እንዲሁም በሴቶች አጠቃላይ ደረጃ 1ኛ በመሆን አጠናቃለች።
በአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር እንጅባራ ከተማ የሚገኘው የአገው ምድር 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በ1990 ዓ.ም ከተመሰረተ ጀምሮ በርካታ ተማሪዎችን ያፈራ ተቋም ነው።
በትምህርት ጉዞውም እውቀትን ከውጤት፣ ውጤትን ደግሞ ከራዕይ ጋር በማገናኘት ለተማሪዎቹ የተሻለ የነገ መንገድ ሲያመቻች ቆይቷል።
ከዚህ ትምህርት ቤት የበቀለችው ተማሪ ሕዳሴ ዘመኑ የዚህ ጥረት ትልቅ ማሳያ ሆናለች። በትምህርት ቤት ቆይታዋ በሁሉም ክፍሎች ከፍተኛ ውጤት ስታስመዘግብ እንደቆየችም መምህሮቻ ይመሰክራሉ።
የሕዳሴ ውጤት በፈተና ቀን ብቻ የመጣ ድገተኛ ስኬት አልነበረም። ከ2014 ዓ.ም ጀምሮ (ከ8ኛ እስከ 11ኛ ክፍል) በእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ STEM ማዕከል የሚሰጡ የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ምህንድስና እና ሂሳብ ስልጠናዎችን በመከታተል የሳይንሳዊ እውቀት አቅሟን ስታጎለብት ቆይታለች።
እንጅባራ ዩኒቨርሲቲ የተማሪዎችን ስኬት እንደ ማህበረሰባዊ ሃላፊነት በመውሰድ ከአዊ ዞን ለተውጣጡ 398 ወንድ እና 295 ሴት በድምሩ ለ693 ተማሪዎች የSTEM ስልጠና ሰጥቷል።
ይህም ዩኒቨርሲቲው ከከፍተኛ ትምህርት ተቋምነቱ ባሻገር የአካባቢውን የነገ ትውልድ አቅም በመገንባት ረገድ የሚጫወተውን አወንታዊ ሚና ማሳያ ሆኗል።
ይህ ስኬት በእንጅባራ ብቻ የሚያበቃ ታሪክ አይደለም፤ ሴት ተማሪዎች በሳይንስ፣ በቴክኖሎጂ፣ በምህንድስናና በሂሳብ (STEM) ዘርፎች የሚያሳዩትን ተሳትፎ ወደ ላቀ ደረጃ ማሸጋገር እንደሚችሉ ያረጋገጠ ታላቅ ምሳሌ ነው።
ለሕዳሴ ዘመኑ ስኬት ትምህርት ቤቷ ያደረገው ድጋፍም የሚጠቀስ ነው። ተማሪዋ የተማረችበት የአገው ምድር 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ከ5 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በማድረግ ደረጃውን የጠበቀ የሳይንስ ላቦራቶሪ አቋቁሟል።
"ሕዳሴ ዘመኑ" ያስመዘገበችው ውጤት ከፈተና ነጥብ በላይ ትርጉም ያለው ሲሆን፣ በትምህርት፣ በሳይንስና በሴቶች ተሳትፎ ላይ የተሰራ የረጅም ጊዜ ጥረት ፍሬ ማፍራቱንም ያሳያል።
በተጨማሪም በተማሪዋ ስም የተሰየመውን “ህዳሴ ቤተመጻሕፍት” በ400 ወንበርና ጠረጴዛዎች እንዲሁም በመጻሕፍት መደርደሪያዎች አሟልቶ ለተማሪዎች አገልግሎት እንዲውል አድርጓል።
በዚህም የሕዳሴ ስም ከውጤት በላይ ትርጉም ይዟል፤ “ህዳሴ” የሚለው ስሟ እንደ ትምህርት ቤቱ ተማሪዎች ህልም እና እንደ አካባቢው የትምህርት ተስፋ መታደስን የሚወክል ሆኗል።
የእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ጋርዳቸው ወርቁ እንደገለጹት፣ ዩኒቨርሲቲው እንደ ሕዳሴ ዘመኑ ያሉ ውጤታማ ተማሪዎችን ለማፍራት በአካባቢው ከሚገኙ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ጋር በቅርበት ለመስራት አቅዶ እየሰራ ይገኛል።
የሕዳሴ አባት አቶ ዘመኑ መምህር ሲሆኑ፣ በከተማው ተማሪዎችን በማፍራት ረገድ ትልቅ አስተዋፅኦ ያበረከቱ ባለሙያ ናቸው።
በትምህርት ቤት ቆይታዋ ከወረዳ ጀምሮ በተካሄዱ የሳይንስ፣ የሂሳብ ትምህርት እና የተለያዩ ውድድሮች ከፍተኛ ውጤት በማምጣት ትምህርት ቤቷንና ወረዳዋን ስትወክል የቆየችው ሕዳሴ፣ በቅርቡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ካስመረቃቸው የSTEM ተመራቂዎች መካከል አንዷ መሆን ችላለች።
በእርግጥም የሕዳሴ ዘመኑ 583 ነጥብ የፈተና ቁጥር ብቻ ሳይሆን፣ ከአንድ ትምህርት ቤት ተነስቶ ወደ ሀገራዊ መድረክ የደረሰ የጥረት ታሪክ ነው። የSTEM ስልጠና፣ የመምህራን ልማት፣ የላቦራቶሪ እና የቤተመጻሕፍት ድጋፍ ተደራጅተው የፈጠሩት የጋራ ውጤት ነው።
ዛሬ፣ ህዳሴ ዘመኑ በታሪክ ላይ ስሟን በጉልህ ጽፋለች። ነገ ግን የእሷ ስኬት በእሷ ብቻ አያበቃም፤ በእሷ ስም የተሰየመው ቤተመጻሕፍት፣ የተገነባው የሳይንስ ላቦራቶሪ እና የተማሪዎች የSTEM ስልጠና ለቀጣዩ ትውልድ የሚተላለፍ የታላቅ ተስፋ ዘር ነው።
በልዩ እሸቱ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: