Search

የጋዛ የሰላም ውል እና የቀይ ባሕር የጂኦ-ፖለቲካ

ረቡዕ ነሐሴ 13, 2018 105

ጥቅምት 2016 . (ኦክቶበር 2024) በደቡብ እስራኤል በተፈጸመው ጥቃት የተቀሰቀሰው እና ሁለት ዓመታትን ተሻግሮ የዘለቀው የጋዛ ጦርነት፣ የመካከለኛው ምሥራቅን የፖለቲካ እና የደኅንነት ካርታ ከሥሩ የቀየረ ታሪካዊ ክስተት ሆኗል።

በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ሕይወት የበላው እና ጋዛን ወደ ፍርስራሽነት የለወጠው ይህ ግጭት፣ 2018 . መጨረሻ አካባቢ በተደረሰው የተኩስ ማቆም ስምምነት የተወሰነ እፎይታ ቢያገኝም፣ ዘላቂ ሰላም ማውረድ ግን አሁንም አልተቻለም።

በአሁኑ ወቅት አሜሪካን ጨምሮ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ግጭቱን ከወታደራዊ ግብግብ ወደ ዘላቂ ፖለቲካዊ መፍትሔ ለማሸጋገር ጥረት እያደረጉ ይገኛሉ።

የዚህ አዲስ የዲፕሎማሲ ምዕራፍ ማዕከል ደግሞ በአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የተቀረጸው ባለ 15 ነጥብ የሰላም ፍኖተ ካርታ ነው።

የፕሬዚዳንት ትራምፕ ከፍተኛ አማካሪ እና የመካከለኛው ምሥራቅ መልዕክተኛ ጃሬድ ኩሽነር በካይሮ ከሐማስ ከፍተኛ አመራር ከኸሊል አል-ሀያ እና ከዓረብ አሸማጋዮች ጋር ያደረጉት ያልተጠበቀ ስብሰባ፣ የዋሺንግተንን የፖሊሲ ዕጥፋት ያሳያል።

አሜሪካ እና እርሷ የምትመራውየሰላም ቦርድየሚያቀነቅኑት መፍትሔ፣ ሐማስ ደረጃ በደረጃ ትጥቁን እንዲፈታ እና እስራኤል በተመሳሳይ መልኩ ወታደሮቿን እንድታስወጣ የሚያስችል ነው።

ኩሽነር ለፖለቲካ ተንታኞች እንደገለጹት፣ ይህ አካሄድ በምድር ላይ ያለውን እውነታ የተቀበለ እንጂ በባዶ መተማመን ላይ የተመሠረተ አይደለም።

ሆኖም ይህ የአሜሪካ ዕቅድ በኢየሩሳሌም በኩል የጠበቀ ፈተና ገጥሞታል። ኩሽነር በኢየሩሳሌም ከእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ጋር ባደረጉት 4 ሰዓታት ረጅም ውይይት፣ ኔታንያሁ በዕቅዱ ላይ ያላቸውን ጥልቅ ጥርጣሬ አንጸባርቀዋል።

ኔታንያሁ የወታደራዊ እና የደኅንነት መሪዎቻቸውን በማቅረብ ሐማስ የተኩስ ማቆም ስምምነቶችን መጣሱን የሚያሳዩ መረጃዎችን ያቀረቡ ሲሆን፣ የእስራኤል አቋም ግልጽ ነው፦ሐማስ ሙሉ በሙሉ ትጥቁን ሳይፈታ ወታደሮቼን አላስወጣም፣ የመልሶ መገንባት ሥራም አይጀመርምየሚል።

የጋዛው ግጭት በስፋቱ ከፍልስጤም እና እስራኤል ወሰን አልፎ አጠቃላይ የመካከለኛው ምሥራቅ እና የቀይ ባሕር ቀጣናን አለመረጋጋት ውስጥ የከተተው ሲሆን፣ በየመኑ የሁቲ አማጽያን በባብ ኤል መንደብ እና በቀይ ባሕር ንግድ መርከቦች ላይ የሚያደርሱት ጥቃት፣ የዓለም አቀፍ ንግድ ፍሰትን በማስተጓጎል አሜሪካ እና ምዕራባውያን አጋሮቻቸውን ለከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ እና ደኅንነት ጫና ዳርጓቸዋል።

በሌላ በኩል እንደ ቻይና እና ሩሲያ ያሉ የብሪክስ አባል ሀገራት፣ ይህን አጋጣሚ በመጠቀም አሜሪካ በመካከለኛው ምሥራቅ ያላትን የበላይነት የሚገዳደር እና አዲስ የመልቲ-ፖላር (Multipolar) ዓለም አቀፍ ሥርዓት ግንባታን ለማፋጠን እየሠሩበት ይገኛሉ።

እንደ  ኢራን እና ሳዑዲ ዓረቢያ ያሉ ቀጣናዊ ሀገራት ወደ ብሪክስ መቀላቀላቸው ደግሞ፣ ዋሺንግተን ቀጣናውን የማረጋጋት ጥረቷን ባጣደፈች ቁጥር ከብሪክስ ሀገራት የሚመጣባትን ጂኦ-ፖለቲካዊ ተፎካካሪነት እንድታስብ አስገድዷታል።

በዚህ ሁሉ መሐል ሐማስ እና ዓረብ ሀገራት ሒደቱን በተለየ መነጽር ይመለከቱታል። ሐማስ ትጥቅ ለመፍታት ፈቃደኛ የሚሆነው እስራኤል ወታደሮቿን ደረጃ በደረጃ ለማስወጣት እና ጥቃቷን ሙሉ በሙሉ ለማቆም በይፋ ስትስማማ ብቻ እንደሆነ አስታውቋል።

ግብጽ፣ ኳታር፣ ቱርክ እና ሳዑዲ ዓረቢያን ጨምሮ ስምንት የዓረብ እና ሙስሊም ሀገራት በጋራ ባወጡት መግለጫ፣ እስራኤል የሰላም ፍኖተ ካርታውን ውድቅ ማድረጓ በጋዛ ያለውን ጦርነት ለማቆም የሚደረገውን ጥረት እንደሚያስተጓጉል አስጠንቅቀዋል።

አሜሪካ እና እስራኤል በትጥቅ መፍታት እና በሰብዓዊ ድጋፍ ዙሪያ የሚሠሩ ሁለት የጋራ ቡድኖችን ለማቋቋም ተስማምተዋል።

ይህም በሁለቱ ወገኖች መካከል ያለውን አለመግባባት በተወሰነ ደረጃ ያቀለለው ቢሆንም፣ የችግሩ ዋና ሥር የሆነውቅድሚያ ትጥቅ መፈታት ወይስ ቅድሚያ ወታደር ማስወጣት?”  የሚለው ጥያቄ ግን አሁንም ምላሽ አላገኘም።

2016 . ጀምሮ ከተቀሰቀሰው አስከፊ ጦርነት በኋላ፣ በቀይ ባሕር ደኅንነት እና በብሪክስ ሀገራት ጂኦ-ፖለቲካዊ ጫና ጥላ ሥር ሆኖ በፕሬዚዳንት ትራምፕ የሰላም ፍኖተ ካርታ ዙሪያ በቀጣዮቹ ሳምንታት የሚወሰዱት ተግባራዊ እርምጃዎች፣ የጋዛ የወደፊት ዕጣ ፈንታ ዘላቂ ሰላም ወይም ዳግም አዙሪት ግጭት መሆኑን የሚወስኑ ይሆናል።

በሰለሞን ገዳ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: