Search

ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የዳልጋ ከብት ዝርያ ማሻሻያ ንቅናቄን በከምባታ ዞን ሀደሮ ከተማ በይፋ አስጀመረ

ሰኞ ነሐሴ 18, 2018 58

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በምክትል ርእሰ መስተዳድር ማዕረግ የገጠር ልማት ክላስተር አስተባባሪና የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ኡስማን ሱሩር፣ በከምባታ ዞን ሀደሮ ከተማ በመገኘት 2019 በሆርሞን ማድራት ባዮቴክኖሎጂ የተቀናጀ የዳልጋ ከብት ዝርያ ማሻሻያ ክልላዊ ንቅናቄን አስጀምረዋል።

በዚሁ ማስጀመሪያ ሥነ ሥርዓት ላይ አቶ ኡስማን እንደገለጹት፣ መንግሥት ግብርናን ለማዘመን እና የየአካባቢውን ዐምቅ ተፈጥሯዊ ጸጋ ወደ ተጨባጭ ሀብት ለመቀየር ባከናወናቸው በርካታ ስትራቴጂካዊ ሥራዎች አመርቂ ውጤቶች ተመዝግበዋል።

ይህም የአርሶ አደሩን የጊዜ፣ የጉልበት እና የመሬት ምርታማነት ከማሳደጉ ባሻገር፣ ከክረምት እስከ ክረምት አረንጓዴ ልማትን እውን በማድረግ ተጨማሪ የልማት ፍላጎት መፍጠር ችሏል።

ኢትዮጵያ በቀንድ ከብት ሀብት በዓለም 5 እንዲሁም በአፍሪካ 1 ደረጃን ብትይዝም፣ ከሀብቱ ልክ ተጠቃሚ መሆን ሳትችል መቆየቷን ያወሱት አቶ ኡስማን፤ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (/) የተጀመረው የሌማት ትሩፋት መርሐ ግብር ከተጀመረ ወዲህ ግን ከቀንድ ቆጠራ ወደ ተጨባጭ ውጤት ቆጠራ መሸጋገር መቻሉን አስረድተዋል።

ባለፉት ሦስት ዓመታት የእንስሳት ዘርፉን ለማዘመን በተሠሩ ሥራዎች በክልሉ ስምንት የወተት ማቀነባበሪያዎችን ማቋቋም የተቻለ ሲሆን፣ ይህም አርቢውንም ሆነ ሸማቹን እኩል ተጠቃሚ አድርጓል።

ሀገራዊ የዝርያ ማሻሻል ሽፋን 3.6 ፐርሰንት በሆነበት ሁኔታ ክልላዊ ሽፋኑ 14.8 ፐርሰንት መድረሱ በዘርፉ መሥራት እንደሚቻል ማረጋገጫ በመሆኑ፣ ይህንኑ አቅም ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ የሁሉም አካላት የተቀናጀና የተናበበ ጥረት እንደሚጠይቅም አሳስበዋል።

የቢሮው ምክትልና የእንስሳትና ዓሣ ሀብት ልማት ዘርፍ ኃላፊ አቶ እያሱ ተረፈ በበኩላቸው፣ በክልሉ ዓመታዊ የወተት ምርትን ወደ 805 ሚሊዮን ሊትር ለማሳደግ እየተሠራ መሆኑንና 287 ሺህ ላሞችን በሰው ሠራሽ መንገድ የማዳቀል ተግባር በመከናወን ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

የከምባታ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ እና የግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ ተሾመ ሄራሞ በዞኑ በሁሉም የግብርና ዘርፎች አበረታች ውጤት መመዝገቡን ጠቁመው፣ በተከናወነው የዝርያ ማሻሻያ ሥራ የወተት ምርትን በመደበኛ አርሶ አደር ደረጃ 18 ሊትር በላይ፣ በሞዴል አርሶ አደር ደረጃ ደግሞ እስከ 39 ሊትር ማድረስ መቻሉን አብራርተዋል።

በሀደሮ ከተማ አስተዳደርና በሀደሮ ጡንጦ ዙሪያ ወረዳ በጋራ በተዘጋጀው በዚህ የሲንክሮናይዜሽን ንቅናቄ ማስጀመሪያ መርሐ ግብር ላይ የክልል፣ የዞንና የልዩ ወረዳ አመራሮች፣ አርሶ አደሮችና ጥሪ የተደረገላቸው ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: