Search

በመካከለኛው ምሥራቅ የፖለቲካ ውጥረት ምክንያት ቻይና “የአርክቲክ በረዶ የሐር መንገድ”ን መጠቀም ጀመረች

ሓሙስ ነሐሴ 14, 2018 81

የመካከለኛው ምሥራቅ የፖለቲካ ውጥረቶች እና በሆርሙዝ እንዲሁም በባብ ኤል-መንደብ የባሕር ወሰኖች ላይ የተፈጠሩት ስጋቶች ዓለም አቀፉን የንግድ እና የሎጂስቲክስ መስመር ፈተና ውስጥ ጥለውታል።

ይህንን ተከትሎ የነዳጅ እና የመድን ዋስትና ወጪዎች በእጅጉ በመጨመራቸው፣ ሀገራት አማራጭ የንግድ መስመሮችን ለማሰስ ተገድደዋል።

የዚህን አጋጣሚ ዕድል በማድረግ ደግሞ ቻይና የዓለምን የንግድ የበላይነት የሚያጎናጽፋትን 5 ሺህ 400 ኪሎ ሜትር በላይ ርዝመት ያለውን እና "የአርክቲክ የበረዶ ሐር መንገድ" (Ice Silk Road) በመባል የሚታወቀውን የሰሜናዊ የባሕር መስመር በስፋት መጠቀም ጀምራለች።

የቻይናው ' ሌጀንድ ላይን' የተሰኘው የመርከብ ኩባንያ በቅርቡ የመጀመሪያውን መደበኛ የንግድ መርከብ ከቻይና የኢንዱስትሪ ማዕከል ከኒንግቦ ተነሥቶ የሩሲያን ሰሜናዊ የባሕር ዳርቻ አቋርጦ ወደ እንግሊዟ ፌሊክስስቶው ወደብ 20 ቀናት ውስጥ ብቻ እንዲደርስ አድርጓል።

ይህም በስዊዝ ካናል በኩል ይወሰድ የነበረውን 40 ቀን በላይ የሚፈጅ ረጅም ጊዜ በግማሽ የሚቀንስ በመሆኑ ከፍተኛ የጊዜ እና የወጪ ብክነትን የሚያስቀር ሆኗል።

ይህ አዲስ የንግድ መስመር እውን ሊሆን የቻለው በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት በአርክቲክ አካባቢ የነበረው የበረዶ ግግር መቅለጥ በመጨመሩ የመርከቦች ዝውውር ምቹ በመሆኑ ነው።

ምንም እንኳን መስመሩ በሩሲያ ቁጥጥር ሥር ያለ እና በዓመቱ ሙሉ በሙሉ ለመጠቀም ገና ተጨማሪ ምልከታዎችን የሚፈልግ ቢሆንም፣ ቻይና በሲንጋፖር ምሥራቅ የባሕር ወሰን ላይ የነበራትን የንግድ ጥገኝነት በመቀነስ ረገድ ትልቅ የጂኦ-ፖለቲካዊ እና የኢኮኖሚ ከለላ ሆኖላታል።

የኩባንያው ሥራ አስፈጻሚዎች በሒደት የመርከቦችን ጉዞ በማስፋፋት አዲሱን የበረዶ መንገድ ዓመቱን ሙሉ ለንግድ እንቅስቃሴ ክፍት ለማድረግ አልመው እየሠሩ ይገኛሉ።

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: