የታላቁ ኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታን ስናስብ ቀድሞ ወደ አእምሯችን የሚመጣው የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት ቢሆንም፣ በግድቡ የውኃ ማከማቸት ሂደት የተፈጠረው ንጋት ሐይቅ ግን አዲስ የኢኮኖሚ እና የምግብ ዋስትና ምዕራፍ ከፍቷል።
እስከ 1 ሺህ 904 ካሬ ኪሎ ሜትር የሚሸፍነው እና ከ74 ቢሊዮን ሜትር ኩብ በላይ ውኃ የመያዝ አቅም ያለው ይህ ግዙፍ ሐይቅ፣ 32.65 በመቶ የሚሆነው ስፋቱ ከ20 ሜትር ያነሰ ጥልቀት ያለው በመሆኑ ለፀሐይ ብርሃን የተጋለጠና ለዓሣዎች መራቢያ እጅግ ምቹ ሥነ-ምህዳር መፍጠር ችሏል።
ከዚሁ ተፈጥሯዊ ጸጋ ጋር ተያይዞ በክልሉ የሚገኘው የዓሣ ምርት አቅም አስገራሚ ዕድገት አስመዝግቧል። ግድቡ ከመገንባቱ በፊት በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የነበረው ዓመታዊ የዓሣ ምርት ከ2 ሺህ 400 ቶን የማይበልጥ የነበረ ቢሆንም፣ አሁን ላይ ግን በዓመት እስከ 14 ሺህ ሜትሪክ ቶን በላይ ማምረት የሚያስችል ሰፊ ዕድል ተፈጥሯል።
በተጨባጭም በአሁኑ ወቅት ከንጋት ሐይቅ የሚገኘው ምርት 10 ሺህ 799 ሜትሪክ ቶን የደረሰ ሲሆን፣ በየዕለቱ ከ14 ሺህ ኪሎ ግራም በላይ ዓሣ እየተመረተ ይገኛል።
ይህም እንቅስቃሴ ከ1 ሺህ 600 በላይ ለሚሆኑ ወጣቶችና በርካታ የዓሣ አጥማጅ ማኅበራት የሥራ ዕድልና የገቢ ምንጭ ሆኗል።
ይሁን እንጂ ይህንን ታላቅ ሀብት በዘላቂነት ለመጠቀምና በቅዝቃዜ ሰንሰለት እጥረት ምክንያት የሚፈጠረውን ብክነት ለማስቀረት ምርቱን ወደ አግሮ-ፕሮሰሲንግ ማሸጋገር ወሳኝ ነው።
በአካባቢው ግዙፍ የማቀነባበሪያ ማዕከል በመገንባት የዓሣ ፊሌት የማሸግ ሥራዎችን ማከናወን፣ ማቀዝቀዣ ለሌላቸው አካባቢዎች ደግሞ ምርቱን አድርቆ ማሰራጨት ይቻላል።
በተጨማሪም ከዓሣው ትራፊ ክፍሎች የፕሮቲን መጠን ያለው የእንስሳትና የዶሮ መኖ በማምረት ዘርፈ-ብዙ ጥቅም ማግኘት ይቻላል።
በመሆኑም ይህ እሴት የሚጨመርበት የዓሣ ሀብት ልማት የዜጎችን የፕሮቲን ፍጆታ ክፍተት በመሙላት የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጡ ባሻገር፣ የታሸጉ ምርቶችን ወደ ጎረቤት ሀገራት በመላክ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ለማስገኘት ያስችላል።
በመጨረሻም የሀብቱ ዘላቂነት እንዳይደፈርስና የዓሣ ዝርያዎች እንዳይጠፉ በሳይንሳዊ ጥናት ላይ የተመሠረተ የማጥመድ ሥርዓትን መከተልና ደንቦችን ማክበር የሁሉም ወገን ኃላፊነት ሊሆን ይገባል።
በለሚ ታደሰ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: