በአሜሪካ እና በኢራን መካከል የተደረገው የ60 ቀናት የተኩስ ማቆም ስምምነት ያለ ምንም ዲፕሎማሲያዊ መፍትሔ መጠናቀቁን ተከትሎ፣ ዋሽንግተን በቴህራን ላይ በታሪክ ታይቶ የማይታወቅ የኢኮኖሚ ዘመቻ ማወጇን አስታውቃለች።
ይህ አዲስ ስትራቴጂ አሜሪካ ቀደም ሲል ከአቪዬሽንና ሚሳይል ጥቃቶች ጋር ተያይዞ የወሰደቻቸው ወታደራዊ እርምጃዎች ከፍተኛ የሰው ህይወትና የገንዘብ ወጪ ከማስከተላቸው ባሻገር የቴህራንን አስተዳደር መስበር ባለመቻላቸው እንዲሁም በሆርሙዝ ሰርጥ ውጥረት ምክንያት የዓለም አቀፍ የነዳጅ ዋጋ በመናሩ የተከተለችው አማራጭ መንገድ ነው።
የአሜሪካው አዲስ ማዕቀብ በኢራን ላይ ብቻ ሳይሆን ከቴህራን ጋር ንግድ፣ የፋይናንስ ወይም የሎጅስቲክስ ግንኙነት በሚያደርጉ የሶስተኛ ወገን ሀገራት፣ በሕገ-ወጥ የነዳጅ ኮንትሮባንድ፣ በገንዘብ ዝውውሮች፣ በሐዋላ ቤቶችና በባህር መርከቦች ምዝገባ ላይ ያተኮረ ቢሆንም፣ የእርምጃው ውጤታማነት ግን ጥያቄ ውስጥ ወድቋል።
የኢራን ዋና ዋና የንግድ አጋሮች የሆኑት ቻይና እና ሩሲያ የአሜሪካን ማዕቀፍ የማክሸፍ ከፍተኛ አቅም አላቸው።
የኢራን ትልቋ የነዳጅ ገዢ የሆነችው ቻይና አብዛኞቹ ነዳጅ የሚያጣሩት የግል ኩባንያዎቿ ከሰሜን አሜሪካ የፋይናንስ ስርዓት ውጭ የሚንቀሳቀሱ በመሆናቸው ለአሜሪካ ማዕቀብ የማይበገሩ ሲሆን፣ ሩሲያ በበኩሏ ከቴህራን ጋር የ20 ዓመት ስትራቴጂካዊ የትብብር ስምምነት በመፈራረም በካስፒያን ባህር በኩል ትይዩ የንግድና የሎጅስቲክስ መስመር ገንብታለች።
በተጨማሪም ኢራን ከዶላር የበላይነት ውጭ በሀገር ውስጥ ገንዘቦች ንግድ ለማድረግ እና ወደ ብሪክስ አዲስ ልማት ባንክ ለመቀላቀል እየሰራች ትገኛለች።
በመሆኑም ወታደራዊ እርምጃዎች ማምጣት ያልቻሉትን የፖለቲካ ለውጥ በኢኮኖሚ ጫና ብቻ ማምጣት አጠራጣሪ ከመሆኑም በላይ፣ ይህ ፍጥጫ በዓለም አቀፍ የነዳጅ ገበያ ላይ ተጨማሪ መወዛወዝን በመፍጠር በዓለም ኢኮኖሚ ላይ የዋጋ ንረት ሸክም የመጫን እድሉ ከፍተኛ ነው።
በሰለሞን ገዳ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: