Search

"ሀገር በቀል እውቀት ለአካባቢ ጥበቃና ለኮሪደር ልማት ስኬት ያለው ሚና ከፍተኛ ነው" ፦ ለሊሴ ነሜ (ዶ/ር)

ቅዳሜ ግንቦት 29, 2018 10

ሀገር በቀል እውቀት ለአካባቢ ጥበቃ ስራ ትልቅ ትርጉም ያለው መሆኑን የኢትዮጵያ የአካባቢ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ለሊሴ ነሜ (/) ገልፀዋል።

 ለዚህም ማሳያ የሚሆነው የኮንሶ ማህበረሰብ በኮሪደር እና በወንዝ ዳርቻ ልማት ላይ እየሰራው ያለው የእርከን ስራ ሀገር በቀል እውቀቶች ምን ያህል ጠቃሚ እንደሆኑ በተግባር የሚያሳይ ነው ብለዋል።

 

ዋና ዳይሬክተሯ አክለውም የአረንጓዴ አሻራ የኮሪደር እና የወንዝ ዳርቻ ልማት ስራዎች ከውበት ባሻገር ለአካባቢ ጥበቃ ትልቅ ትርጉም ያላቸው መሆኑን አስገንዝበዋል።

ለአየር ንብረት ለውጥ ዋነኛ መነሻው የአየር ብክለት መሆኑን የጠቀሱት ዶክተር ለሊሴ ኢትዮጵያ በእነዚህ የልማት ስራዎች እያከናወነች ያለችው ተግባር የአየር ንብረት ለውጥን በመከላከል ረገድ ትርጉም ያለው ለውጥ እያመጣች መሆኑን አብራርተዋል።

በሌላ በኩል በኮሪደር ልማት ስራዎች ለሞተር አልባ ተሽከርካሪዎች አስቻይ ሁኔታ መፈጠሩ ወደ አየር የሚላከውን በካይ ጋዝ በእጅጉ የሚቀንስ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአካባቢ ባለስልጣን ዋና ስራ አስኪያጅ ዶክተር እሸቱ ለማ ገልጸዋል።

ዋና ስራ አስኪያጁ አክለውም በወንዝ ዳርቻ ልማት አማካኝነት ወንዞች ከቆሻሻ ማስወገጃነት ተቀይረው የቱሪዝም መዳረሻ መሆን መቻላቸውን ጠቁመዋል።

እንደ ከተማ አስተዳደርም በሁለት ዋና ዋና ወንዞች እና በስምንት ገባሮች በተሰራ የልማት ስራ 49 ኪሎ ሜትር የወንዝ ዳርቻ ማልማት ተችሏል።

የአካባቢ ጥበቃ ቀን በዓለማቀፍ ደረጃ 53 ጊዜ በኢትዮጵያ ደግሞ 33 ጊዜ እየተከበረ ይገኛል።

ይህንን የእለቱን መታሰቢያ ምክንያት በማድረግም የፌደራል እና የከተማ የአካባቢ ባለስልጣን አመራሮች ባለሙያዎች እንዲሁም የዓለም አቀፍ አጋር ድርጅት ተወካዮች በቅርቡ ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት የሆነውን የእንጦጦ ፒኮክ የወንዝ ዳርቻ ልማትን በጋራ ጎብኝተዋል።

በመስከረም ቸርነት