በኦሮሚያ ክልል በዘንድሮው ዓመት 370 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ 2.8 ቢሊየን የቡና ችግኝ እንደሚተከል የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።
በጅማ ዞን ማና ወረዳም የዘንድሮው የቡና ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር በይፋ ተጀምሯል።
መርሃ ግብሩን ያስጀመሩት የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ ጌቱ ገመቹ ፤ የተሻሻሉ የቡና ዝርያዎችን ለአርሶ አደሩ በማቅረብ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የተሰራው ስራ ውጤት እያመጣ ነው ብለዋል።
ዘንድሮ 2 ነጥብ 8 ቢሊየን የቡና ችግኞች ተዘጋጅተው በ370 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ እየተተከሉ መሆኑንና ይህም የክልሉን አጠቃላይ የቡና ምርት ሽፋን ወደ 3 ነጥብ 5 ሚሊየን ሄክታር እንደሚያሳድገው መግለፃቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
በቀጣይም ምርታማነቱን ይበልጥ ለማሳደግ ከግብርና ምርምር ማዕከላት ጋር በመተባበር የተሻሻሉ ዝርያዎችን የማቅረቡ ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ተብሏል።