የአማራ ክልል ሚሊሻ ኮሚሽን የተመሰረተበትን 30ኛ ዓመት በዓል ማጠቃለያ መርሃ ግብር በባሕር ዳር ከተማ ባካሄደበት ወቅት፥ ሚሊሻ የኢትዮጵያን ክብር እንደ ደመወዝ፣ የሕዝብን ሰላም ደግሞ እንደ ሽልማት የቆጠረ የሀገር ዋስትና መሆኑን የክልሉ ርዕሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ ገለጹ።
ርዕሰ መስተዳድር አቶ አረጋ ከበደ እንደተናገሩት፥ የሚሊሻ ኃይል ከሕዝብ አብራክ የወጣ፣ ከትንሿ መንደር እስከ ታላቋ ሀገር ድረስ ሰላምን የሚጠብቅ እና ራሱን ለልማት የሰጠ ሁነኛ የሰላም ዘብ ነው።
ይህ የጸጥታ አካል በሰላም ጊዜ በልማት ሥራዎች ላይ በንቃት የሚሳተፍ ሲሆን፥ ሀገር ተደፈረች በተባለ ጊዜ ግን የግል ምቾቱን ወደ ጎን በመተው በራሱ ትጥቅና ስንቅ ግንባር ቀደም ሆኖ የሚሰለፍ በመሆኑ ለሀገር ነጻነትና ሉዓላዊነት በደማቁ የተጻፈ ታሪክ እንዳለው አብራርተዋል።
የሚሊሻ የ30ኛ ዓመት የምስረታ በዓል መከበር አገልግሎቱ ከሦስት አስርት ዓመታት በፊት ተጀመረ ማለት ሳይሆን፥ በክልሉ መደበኛ መዋቅርና አሰራር ተዘርግቶለት የተቋቋመበትን ጊዜ ለመዘከር መሆኑን ርዕሰ መስተዳድሩ አስገንዝበዋል።
የሚሊሻ እውነተኛ የአገልግሎት ዘመን የሀገርን ክብር ከትውልድ ወደ ትውልድ ያሻገረ የረጅም ዘመናት ታሪክ ያለው መሆኑን የጠቀሱት አቶ አረጋ፤ የክልሉ የሚሊሻ ኃይል በቅርብ ጊዜያትም የሕዝብን ሰላም ለማናጋት የተንቀሳቀሱ ላኪና ተላላኪዎችን በመመከት ረገድ ከፍተኛ ተጋድሎ ማድረጉን አስታውሰዋል።
አሁንም ቢሆን የሕዝብን ደህንነት ለመንካት የሚጥሩ የውስጥና የውጭ ጠላቶች መኖራቸውን በመጠቆም፥ የሚሊሻ ኃይሉ አካባቢውን በንቃት በመጠበቅና ከሌሎች የጸጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት የሰላም ዋስትናነቱን አጠናክሮ እንዲያስቀጥል ማሳሰባቸውን አሚኮ ዘግቧል።
የክልሉ መንግሥት ለሚሊሻ አባላት የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ያረጋገጡት ርዕሰ መስተዳድሩ፥ መላው ሕዝብም ለሰላሙ ዘብ ለሆኑት ለእነዚህ የሕዝብ አገልጋዮች ተገቢውን ክብርና እንክብካቤ ሊሰጣቸው እንደሚገባ ተናግረዋል።