በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና መሥሪያ ቤት በተካሄደው የ2026ቱ ዓለም አቀፍ የሰላም አስከባሪዎች ቀን መታሰቢያ ላይ፤ ለዓለም ሰላም ሲሉ ሕይወታቸውን ላጡ የኢትዮጵያ ሠራዊት አባላት ታሪካዊ መስዋዕትነት ታላቅ ክብር ተሰጥቷል።
ከተመድ መሥራች ሀገራት መካከል ግንባር ቀደም የሆነችው ኢትዮጵያ፤ ላለፉት በርካታ አስርት ዓመታት በዓለም አቀፍ የሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች ላይ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሠራዊት በማሰማራት ያሳየችው ቁርጠኝነት በዓለም አቀፉ መድረክ በጉልህ ተመስክሮለታል።
ሰሞኑን የተከበረውን ዓለም አቀፉን የሰላም አስከባሪዎች ቀን ምክንያት በማድረግ፤ የተመድ ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ የሰላም ጥበቃ ሥራ ከተጀመረበት ከዛሬ 80 ዓመታት ወዲህ ሕይወታቸውን ላጡ 4 ሺህ 500 ለሚጠጉ የሰላም አምባሳደሮች የአበባ ጉንጉን አኑረዋል።
ከታሪካዊው የኮሪያ ዘመቻ ጀምሮ ዘመናትን የተሻገረ የሰላም አሻራ ያላት ኢትዮጵያ፤ በአሁኑ ወቅትም በአፍሪካ እና በአጎራባች ሀገራት ሰላምና መረጋጋትን ለማስፈን ወታደራዊ፣ ፖሊስ እና ሲቪል ባለሙያዎችን በቁርጠኝነት በማሰማራት ግንባር ቀደም ሀገር ሆና ቀጥላለች።
ዋና ጸሐፊው በቅርቡ በአስቸጋሪ ግዳጆች ላይ እያሉ መስዋዕትነት ለከፈሉ የተለያዩ ሀገራት 68 የሰላም አስከባሪዎች የዳግ ሀመርሾልድ ሜዳሊያን ከሞት በኋላ (Posthumously) በክብር አበርክተዋል።
የተመድ ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ባስተላለፉት መልዕክት፥ "እነሱ የሰውን ልጅ ምርጥ ሰብዓዊነት የሚወክሉ ናቸው፤ የሌሎችን ደኅንነት ለመጠበቅ ሲሉ ማንኛውንም ነገር ለአደጋ ለማጋለጥ የተዘጋጁ ሰዎች" ሲሉ የሰማዕታትን የላቀ ታሪክ አወድሰዋል።
በተመድ ዋና መሥሪያ ቤት በተካሄደው በዚህ ልዩ ሥነ ሥርዓት ላይ የዳግ ሀመርሾልድ ሜዳሊያን ጨምሮ፣ የዓመቱ ምርጥ የተመድ ሴት ፖሊስ መኮንን፣ የዓመቱ ምርጥ የተመድ ወታደራዊ የሥርዓተ-ፆታ ተሟጋች እና ለልዩ ጀግንነት የሚሰጠው የካፒቴን ምባዬ ዲያኝ ሜዳሊያ ሽልማቶች ተበርክተዋል።
የዓለም የሰላም አስከባሪዎች ቀን፥ ለሰላም ዓላማ ሲሉ ሕይወታቸውን የሰጡትን በክብር ለማስታወስ እንዲሁም በታሪክ ዘመናት የነበሩትንና በአሁኑ ወቅትም በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ ሆነው የሰውን ልጅ ደኅንነት ለመጠበቅ በማገልገል ላይ ያሉ የተመድ ሰላም አስከባሪዎችን ውድ አበርክቶ እውቅና ለመስጠት በየዓመቱ ይከበራል።
በላሉ ኢታላ