የሀገረ መንግሥት ግንባታ ጉዟችንን በጽኑ መሠረት ላይ ለማቆም፣ ከስሜታዊነት ይልቅ ምክንያታዊነትን ማስቀደም የግድ ይላል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የተጻፈው "የመደመር መንግሥት" መጽሐፍ እንደሚያስገነዝበው፣ መደመር ከአክራሪ ማንነቶች በመውጣት በሐሳብ የበላይነት ላይ የቆመ ፖለቲካን ይከተላል።
ይህ መርሕ በጠበበ ማንነት እና በፅንፈኝነት ላይ የተመሠረቱ የፖለቲካ አካሄዶች ለኢትዮጵያ ሕልውና እና አንድነት ትልቅ አደጋ መሆናቸውን በግልጽ ያሳያል።
አክራሪ ማንነቶች በልዩነቶች ላይ ብቻ በማተኮር ማኅበራዊ ትስስርን የሚያላሉ እና ግጭትን የሚጋብዙ ናቸው።
ሀገራችን ከዚህ አዙሪት ወጥታ በሐሳብ ገዢነት እና በምክንያታዊነት ላይ የተመሠረተ የፖለቲካ ሥርዓት መገንባት ይኖርባታል።
ፖለቲካ በጥላቻ ላይ የተመሠረተ ስሜታዊ መድረክ ሳይሆን በሕዝቦች መካከል ሀገራዊ ስምምነትን እና ገዢ ትርክትን የሚፈጥር የሐሳብ ገበያ መሆን እንዳለበት የመደመር መንግሥት ጽኑ አቋም አለው።
እውነተኛ ሰላም፣ ዕድገት እና ዘላቂ ብልፅግና የሚረጋገጡት በጠመንጃ አፈሙዝ ወይም በኃይል አማራጭ ሳይሆን፣ በሰለጠነ መንገድ በጠረጴዛ ዙሪያ በሚደረግ ውይይትና ምክክር ብቻ ነው።
የጦርነት እና የግጭት አካሄድ ሁሉንም ተሸናፊ የሚያደርግ የጥፋት መንገድ ነው። በጠረጴዛ ዙሪያ የሚደረግ ውይይት ግን ለሁሉም ወገኖች እኩል ዕውቅና የሚሰጥ፣ ፍላጎቶችን የሚያስማማ እና እያንዳንዱን ዜጋ አትራፊ የሚያደርግ አስተማማኝ ጎዳና ነው።
መንግሥት ይህን የተቀደሰ ዓላማ ማዕከል በማድረግም ዋነኛ ትኩረቱን ውይይትን፣ እርቅን እና የሰላም አማራጮችን ማስፈን አድርጎ እየሠራ ይገኛል።
የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ተቋቁሞ በሥራ ላይ ሲሆን፣ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲም ወጥቶ ዝግጁ ሆኗል።
ይህም መንግሥት ውይይትን፣ እውነትን እና የሐሳብ የበላይነትን የመፍትሔዎች ሁሉ ማዕከል አድርጎ እየተንቀሳቀሰ ለመሆኑ ግልጽ ማሳያ ነው።
ከሀገራዊ ምክክር መድረኩ የሚፈልቁ የፖሊሲ ምክረ ሐሳቦችን በቅንነት ለመቀበል እና ተግባራዊ ለማድረግ መንግሥት ዝግጁ መሆኑን በተደጋጋሚ መግለጹም ለተፈጻሚነቱ ያለውን ቁርጠኝነት ያረጋግጣል።
በመሆኑም እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ለሰላም እና ለውይይት ራሱን ማዘጋጀት ይኖርበታል።
በፍቅር፣ በወንድማማችነት እና በዕውቀት ላይ የቆመውን "የመደመር መንግሥት" እሳቤን መላበስ እና በተግባር መተርጎም ይገባል።
ያለፈ ታሪካችንን በመነቃቀፍ እና በጥላቻ ለመተራመስ ለማዋል ሳይሆን፣ ካለፉ ስህተቶቻችን ተምረን የጋራ እሴቶቻችንን በማጎልበት የተሻለች ኢትዮጵያን ለመገንባት ሁላችንም በጋራ መቆም አለብን።
በጠመንጃ ኃይል የሚመጣ ዘላቂ ድል እንደሌለ እስከአሁን ከመጣንበት ታሪካችን በላይ ቋሚ ምስክር አይኖርም።
ዘላቂ እና አስተማማኙ ድል የሚገኘው ልዩነቶቻችንን በውይይት እና በሀሳብ የበላይነት መፍታት ስንችል ብቻ ነው።
ሁላችንም የሰላም መልዕክተኞች እና የውይይት ጀማሪዎች በመሆን ለነገዋ የበለጸገች ኢትዮጵያ የበኩላችንን አዎንታዊ አሻራ እናኑር!
በለሚ ታደሰ