ኢትዮጵያ በታሪኳ አካታች የተባለለትን ሀገራዊ ምክክር እያካሄደች ትገኛለች።
ባለፉት ዓመታት ከተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎችን በማሳተፍ አጀንዳ ሲያሰባስብ የቆየው የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አሁን ወደ ዋናው እና የማጠቃለያው ምዕራፍ እየተሸጋገረ ነው።
ይህ ሂደት በረጅሙ የኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ እንደ ትልቅ አጋጣሚ የሚታይ ወርቃማ ዕድል ነው።
ይህን ዕድል በአግባቡ መጠቀም ከተቻለ፣ ኢትዮጵያን ለዘመናት ሲፈታተናት ከኖረው የግጭት አዙሪት አውጥቶ አዲስ ብሩህ ጊዜ የሚያመጣላት ነው።
በበርካታ ጩኸት እና ወከባ መካከል ታሪካዊ ምርጫ በማካሄድ ለሀገራቸው ያላቸውን ፍቅር የገለጹት ኢትዮጵያውያን፣ የምክክሩን ሂደትም በውጤታማነት እንደሚያጠናቅቁት አይጠረጠርም።
በአንድ ሀገር ታሪክ ውስጥ የፖለቲካ ዋልታ ረገጥነት ሲገነግን እና ሥር የሰደዱ ታሪካዊ ቅሬታዎች ከፍተኛ ደረጃ ላይ ሲደርሱ የሀገር ሕልውና ፈተና ላይ ይወድቃል። ይህም የተለያዩ ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ ቀውሶችን ያስከትላል።
እነዚህን ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ ቀውሶች በመቀልበስ ሀገራዊ ሕልውናን ጠብቆ ለማቆየት የተለያዩ አማራጮችን መጠቀም የተለመደ ነው።
ከእነዚህ አማራጮች መካከል በርካታ ሀገራት ከከፋ ብሔራዊ የመበታተን አደጋ ራሳቸውን የታደጉበት ዋነኛው ስትራቴጂያዊ መፍትሔ ሀገራዊ ምክክር ነው።
የሀገራዊ ምክክር መድረክ የፖለቲካ ልሂቃን ጊዜያዊ ስምምነት ሳይሆን የአንድን ሀገር የወደፊት ዕጣ ፈንታ በጽኑ መሰረት ላይ ለመገንባት የሚያገለግል የሕልውና ዋስትና ነው።

የሀገራዊ ምክክር ዋነኛው እና ቀዳሚው አስፈላጊነት፣ የኃይል አማራጭን ሙሉ በሙሉ በመግታት የሀሳብ የበላይነትን ማረጋገጥ መቻሉ ላይ ነው።
በተለይም የተለያዩ የፖለቲካ ኃይሎች ፍላጎቶቻቸውን በኃይል ወይም በጦርነት ለማስፈጸም በሚሞክሩበት በአሁኑ ወቅት፣ ምክክሩ ጠመንጃን አስቀምጦ በጠረጴዛ ዙሪያ በመወያየት የመደማመጥ ዕድልን ይፈጥራል።
ይህ ሂደት ማኅበረሰቦችን ከአውዳሚ ጦርነት አውጥቶ፣ ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ የመፍታት አዲስ የፖለቲካ ባህልና ሥነ-ልቦና ለመቅረጽ ትልቅ አጋጣሚ ነው።
ምክክሩ ሁሉም ድምጹን የሚያሰማበት አካታች መድረክ መሆኑም ዘላቂ መፍትሔ ለማምጣት ጽኑ መሠረት ነው።
ሀገራዊ ቀውሶች የሚፈጠሩት በዜጎች እና በመንግሥት መካከል ያለው ግንኙነት ሲሻክር ወይም ነባር የሕግ እና የፖለቲካ መዋቅሮች ሁሉንም እኩል ማስተናገድ ሲያቅታቸው ነው።
ሀገራዊ ምክክር ዜጎች በወል እሴቶቻቸው፣ በሀገራዊ አርማዎቻቸው እና በወደፊት የጋራ ዕጣ ፈንታቸው ላይ ተወያይተው አዲስ ማኅበራዊ ውል እንዲቀርጹ ዕድል ይሰጣል።
በተለይ በዚህ የዲጂታል ሚዲያ ዘመን የተዛቡ ትርክቶች እና ጽንፍ የያዙ የፖለቲካ አመለካከቶች በማኅበረሰቦች መካከል ጥርጣሬን እና ጥላቻን የመዝራት አቅም አላቸው።
ሀገራዊ ምክክር በዚህ መልኩ የተቃረኑ የፖለቲካ ኃይሎች እና የኅብረተሰብ ክፍሎች ፊት ለፊት ተገናኝተው እንዲደማመጡ ያደርጋል።
ይህም ለዘመናት የዘለቁ ታሪካዊ ቁርሾዎችን ለመፈወስ፣ የጋራ እውነትን ለመፈለግ እና በጥርጣሬ የተሞላውን ምኅዳር ወደ መተማመን ለመቀየር የሚረዳ ፍቱን መድኃኒት ነው።
በአግባቡ ከተጠቀሙበት፣ ምክክር ለሀገር ያለው አስፈላጊነት ከሰላም መድረክነት የላቀ ነው።
ምክክር ሀገርን ከትርምስ አውጥቶ በጽኑ መሠረት ላይ መልሶ የመገንቢያ ሁነኛ መሳሪያ ነው።
ማረጋገጥ የሚያሻን ሂደቱ ሁሉን አቀፍ እንዲሁም ከፖለቲካ ጣልቃ ገብነት የጸዳ፣ ገለልተኛ መሆኑን ብቻ ነው።
በሔዋን ጌታቸው