Search

የነፃነት ማኅተም፦ ከተረጂነት ወደ አምራችነት

ሰኞ ሰኔ 01, 2018 110

(የዕለቱ መልዕክት)

ኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ዕድገት ለማረጋገጥ እና ታላቅነቷን በጽኑ መሠረት ላይ ለመገንባት በሚደረገው ታሪካዊ ጉዞ ውስጥ፣ የምግብ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ የብሔራዊ ክብር እና የሀገር ሉዓላዊነት ዋነኛ መገለጫ እየሆነ መጥቷል።

ያለፉት ዘመናት መከራ እና የዕርዳታ ጥገኝነት ዛሬ ላይ የውስጥ አቅማችንን እንድንፈትሽ እና ወደ አዲስ የአርበኝነት ምዕራፍ እንድንሻገር ብርቱ ቁጭትን ፈጥሮብናል።

የሀገር ሉዓላዊነት የሚጸናው ድንበር ከመጠበቅ ባሻገር በምግብ ራስን በመቻል፣ በቴክኖሎጂ እና በበጀት ሉዓላዊነት ምሰሶዎች ላይ መሆኑን በተግባር የተረዳንበት ወቅት ላይ እንገኛለን።

ይህን ታላቅ ዓላማ ለማሳካት ደግሞ ከተረጂነት መንፈስ ተላቅቆ ወደ ምርታማነት መሸጋገርን የሚጠይቅ አዲስ ዓይነት የኢኮኖሚ ዐርበኝነት የግድ ያስፈልገናል።

ሀገራችን ከተረጂነት ወደ ምርታማነት በሚለው መሪ ዕሳቤ መሠረት፣ ሰብዓዊ ድጋፍን ከውጭ ጥገኝነት አላቅቆ ወደ ዘላቂ አምራችነት የሚያሸጋግር የክብር መርሐ ግብር በቁርጠኝነት ወደ ተግባር አስገብታለች።

በሴፍቲኔት የሚደገፉ ዜጎች ከተረጂነት ወጥተው ራሳቸውን እንዲችሉ የሚያደርጉ የድጋፍ እና የሥራ ዕድል የመፍጠር ሥራዎች በስፋት ተከውነዋል።

ክልሎች እና ዞኖች የራሳቸውን የምግብ መጠባበቂያ እንዲያዘጋጁ መደረጉም፣ ድንገተኛ አደጋዎችን በራስ አቅም ለመቋቋም የሚያስችል ትልቅ መዋቅራዊ አቅም ፈጥሯል።

ይህ የሉዓላዊነት ጉዞ በምግብ ብቻ ሳይሆን ሀገራችን በመድኃኒት ምርትም ራሷን እንድትችል የሚደረገውን ጥረት ያጠቃልላል። ያለንን የተፈጥሮ ጸጋ እና አቅም ወደ ተጨባጭ ምርት ለመቀየር በተደረገው የላቀ ጥረት በስንዴ ልማት መርሐ ግብር ኢትዮጵያን ከተመጽዋችነት እና ከልመና ታሪክ ያወጣ ታሪካዊ ስኬት ተመዝግቧል።

ይህን መልካም ተሞክሮ በሌሎች የግብርና ዘርፎችም ለመድገም በሩዝ፣ በአትክልት እና ፍራፍሬ፣ በሻይ ቅጠል እና በሌሎች ሰብሎች ላይ እየተከናወኑ ያሉት ሥራዎች አበረታች ውጤት እያስገኙ ይገኛሉ።

የቀጣይ ዓመታት የመንግሥት ዋና ተግባር የሚሆነውም በሀገር ደረጃ የሚካሄደውን የሰብዓዊ ድጋፍ አሰጣጥ በማጠናከር፣ በተፈጥሮ እና በሰው ሠራሽ አደጋዎች የሚመጡ ችግሮችን በራስ አቅም የመፍታት ሥራዎች ላይ ማተኮር እንደ ሆነ ተነግሯል።

ይህም የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት የሚያረጋግጥ ስትራቴጂያዊ የምግብ ክምችት በሁሉም ደረጃ እንዲኖር ያስችላል።

ከዚህም አልፎ፣ ኢትዮጵያዊ ድጋፍ ለኢትዮጵያውያን በኢትዮጵያዊነት የሚለው የትብብር ማዕቀፍ እየተጠናከረ ይሄዳል። ለዚህም በመገባደድ ላይ ባለው የበጀት ዓመት መጨረሻ ሰብዓዊ ድጋፍን ሙሉ በሙሉ በሀገር ውስጥ አቅም ለመሸፈን በትጋት እየተሠራ ነው።

ይህ ተግባር የጥገኝነትን እና የልመናን የቆየ ፖለቲካዊ ዕሳቤ ሙሉ በሙሉ የሚሽር፣ የኢትዮጵያን የአምራችነት እና የማንሰራራት ወርቃማ ዘመን የሚያበሥር ነው።

የታሪክ አውራ የሆነችው ሀገራችን ኢትዮጵያ በርካታ ያልተነኩ ጥሬ ሀብቶች፣ ተስማሚ የአየር ንብረት እና ለሥራ ትጉ የሆነ ሰፊ የወጣት ኃይል የታደለች ናት። ሁላችንም እጅ ለእጅ ተያይዘን፣ በቁጭት እና በቁርጠኝነት ሌት ተቀን ካመረትን የማይታለፍ አቀበት፣ የማይሸነፍ የድህነት ታሪክ አይኖርም።

ብሔራዊ መጠባበቂያን በማደራጀት እና አዳዲስ ፖሊሲዎችን በመተግበር፣ ኢትዮጵያ አምራች ሀገር ሆና በምግብ ሉዓላዊነቷ የተከበረች እንድትሆን ማድረግ ከሁላችንም ይጠበቃል።

እስካሁን ሀገራችንን ከጠላቶቿ ለመጠበቅ እና ሉዓላዊነቷን ለማስከበር የደም ዋጋ ጭምር ከፍለን እንዳቆየናት ሁሉ፣ በቀጣይም ሌት ተቀን ሠርተን በማምረት ሀገራችንን ከምግብ ተረጂነት እና ከጥገኝነት ማላቀቅ የታሪካዊ ግዴታችን ማኅተም ሊሆን ይገባል።

የኢቢሲ ዶትስትሪም ኤዲቶሪያል