Search

የምናብ ጉልበት፡ የተነጣጠሉ ነጥቦች ወደ ገዘፈ የከተማ ሥዕል ሲቀየሩ

ማክሰኞ ሰኔ 02, 2018 123

የሰው ልጅ አዕምሮ ከሚመካባቸው ጸጋዎች ሁሉ አቻ የማይገኝለት ትልቁ እና ድብቁ ኃይል ማሰብ' ወይም አስቀድሞ የማለም (The Power of Imagination) ጉልበት ነው።

አንድን ታላቅ ሥራ በአካል እና በመሬት ላይ ከመሠራቱ በፊት በሐሳብ አጠናቅቆ ማየት፣ መሬት ላይ ከመቆሙ በፊት በአዕምሮ ጓዳ ገንብቶ መጨረስ የትልቅ ራዕይ እና የላቀ አመራር መገለጫ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (/) ከዛሬ ስድስት እና ሰባት ዓመታት በፊት አዲስ አበባን በተመለከተ ያጋሩን ራዕይ ይህንኑ የማለም ጉልበት በትክክል የሚያሳይ፤ ቃልን ወደ ተግባር የመቀየርን አቅም በተጨባጭ ያረጋገጠ ሕያው ምስክር ነው።

አዲስ አበባ የአፍሪካ የፖለቲካ ማዕከል እንዲሁም የሀገራችን የንግድ እምብርት መሆኗ ታሪካዊ ክብር አለው። ይሁን እንጂ፣ ይህ ስሟ እና ክብሯ ከከተማዋ ነባራዊ ገጽታ ጋር ለዘመናት ሲጣረስ ቆይቷል።

ከተማዋ ለነዋሪዎቿ የተመቸች፣ አረንጓዴ እሴትን ያላበሰች እና ሥነ ውበቷ እጅግ የተጠበቀ መዲና እንድትሆን ማድረግ ከምኞት ባለፈ ተጨባጭ ዕቅድ እና የምናብ ጉልበት ይፈልግ ነበር።

ይህንን ትልቅ ሕልም መሬት ላይ ለማውረድ የተመረጠው ስትራቴጂ፣ በአንድ ጊዜ ሁሉንም ከማተራመስ ይልቅ፣ ልክ እንደ ታላቅ ሠዓሊ ከተማዋን ውብ ለማድረግ ትንንሽ ነጥቦችን (Dots) በተለያዩ ቦታዎች ላይ ማስቀመጥ ነበር።

በወቅቱ እነዚህ ነጥቦች ለብቻቸው ሲታዩ የየራሳቸው ውበት ቢኖራቸውም፣ ወደፊት ምን ዓይነት ትልቅ ሥዕል እንደሚፈጥሩ ለመገመት ግን ያንኑ 'የምናብ ኃይል' ይጠይቅ ነበር።

እያንዳንዱ የልማት ሥራ የየራሱን ደማቅ ነጥብ በከተማዋ ገጽ ላይ አኖረ። መጀመሪያ ላይ በከተማዋ አናት ላይ የተቀመጠ፣ አረንጓዴ እሴትን ከተፈጥሮ ውበት ጋር ያዋሃደ እና ለከተማዋ ሳንባ የሆነ ጉልህ ነጥብ የሆነው እንጦጦ ፓርክ እንዲሁም የሀገራችንን ታሪክ፣ ፖለቲካዊ ውጣ ውረድ እና እምቅ ሀብት በአንድ ላይ ያሰናሰለው የአንድነት ፓርክ ተገነቡ።

ይህ ነጥብ የከተማዋን ታሪካዊ እና ሥነ ሕንፃዊ ውበት አጉልቶ አሳየ። በመቀጠልም የወዳጅነት ፓርክ፣ አብርሆት ቤተ መጽሐፍት፣ የመስቀል አደባባይ፣ የሳይንስ ሙዚየም፣ እና የአንድነት ፓርኪንግ እያለ ነጥቦቹ በየቦታው መቀመጣቸውን ቀጠሉ።

እነዚህ ትንንሽ የሚመስሉ ግን ግዙፍ ትርጉም ያላቸው ነጥቦች፣ በከተማዋ የተለያዩ አቅጣጫዎች እንደ ብሩህ ከዋክብት ማብራት ጀመሩ። የነዋሪውን የሥነ ልቦና ከፍታም አብረው አነጹ።

የከተማዋ አስተዳደር ማዕከል የሆነው ታሪካዊው የአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት ዕድሳት ተደርጎለት ዘመናዊ እና ለአገልግሎት ምቹ ሲሆን፣ ከዚያ ተነሥቶ እስከ መስቀል አደባባይ የተዘረጋው ልማት ከተማዋን ወደ አዲስ የዕይታ ምዕራፍ አሸጋገራት።

በእያንዳንዱ ማዕዘን የታየው የከተማዋ የቀለም ቅብ፣ የሕንፃዎች መስተጋብር እና የብርሃን ድምቀት፣ ነጥቦቹን እርስ በእርስ ማስተሳሰር እና ውብ ቅርጽ መስጠት ጀመረ። ምንም እንኳ ገና ሙሉ ምሥሉን ማየት ባይቻልም ማለት ነው።

የዚህ ሁሉ ታላቅ ሥራ መሰብሰቢያ እና በተበታተነ መልኩ የተቀመጡትን ነጥቦች በሙሉ አገናኝቶ አስቀድሞ የታለመውን ሥዕል ገሀድ ያደረገው ደግሞ ትልቁ የኮሪደር ልማት እና የወንዝ ዳርቻ ፕሮጀክቶች ናቸው።

የተለያዩ የከተማዋን ክፍሎች ከዋና ዋና ማዕከላት፣ እንጦጦን ከወንዝ ዳርቻዎች ጋር የሚያስተሣሥሩት እነዚህ የኮሪደር መንገዶች፣ የከተማዋን የደም ሥሮች አጸዱ።

ከኮሪደር ልማቱ ጎን ለጎን የተሠራው የወንዝ ዳርቻ ልማት ደግሞ ከተማዋን ከቆሻሻ ገንዳነት ወደ ማራኪ የመዝናኛ ስፍራነት ቀየራት። አሁን እያንዳንዱ 'ዶት' ሲገጣጠም፣ አስቀድሞ በጠቅላይ ሚኒስትሩ አዕምሮ ውስጥ ተሥሎ የነበረው የተሟላ የከተማ ገጽታ በዐይናችን ፊት ድቅን አለ።

ዛሬ ላይ ቆመን ወደ ኋላ ስንመለከት፣ ቀድሞ የማየት ብቃት፣ በሐሳብ ውስጥ የመጨረስ አቅም፣ እና ቃልን ወደ ተግባር የመቀየር ጉልበት ምን ያህል ድንቅ እና ፈታኝ እንደነበረ እንረዳለን።

መጀመሪያ ላይ "የማለምን ጉልበት" በትክክል የተረዳው አመራር፣ እያንዳንዱ ነጥብ ሲገናኝ የሚፈጥረውን ትልቅ እና ማራኪ ሥዕል አስቦት ነበር። ነጥቦቹ ሲገጣጠሙ የፈጠሩት ሥዕል፣ አዲስ አበባን በአዲስ መልክ አዋቅሯታል።

የከተማዋ ገጽታ የተሟላ መልክ ይዟል፤ አረንጓዴነቷ ደምቋል፤ ለመኖሪያ፣ ለሥራ፣ ለንግድ እና ለዲፕሎማሲ ያላት ተመራጭነት እና ምቾት በከፍተኛ ደረጃ አድጓል።

የማለም ጉልበት ማለት ባዶ ምኞት ወይም ከእውነት የራቀ ሕልም አይደለም። ራዕይን ነድፎ፣ እያንዳንዱን እርምጃ በስሌት አስቀምጦ፣ ተግዳሮቶችን ተቋቁሞ፣ ትንንሽ ነጥቦችን በተግባር ወደ ትልቅ ሥዕል የመቀየር ጥበብ ነው።

ዛሬ ላይ በአዲስ አበባ ጎዳናዎች ስንራመድ፣ በፓርኮቿ ስንዝናና፣ በዘመናዊ ኮሪደሮቿ ስናልፍ የምናየው የድንጋይ፣ የአስፋልት እና የሲሚንቶ ክምችት ሳይሆን፣ የዳበረ የማሰብ አቅም ወደ ተጨባጭ ተግባር ሲቀየር የሚፈጠረውን ሕያው ምሥክር ነው።

ይህ ከአራት እና አምስት ዓመታት በፊት የታለመው ራዕይ ፍሬ፣ በእርግጥም የማለም ኃይል ሀገርን እና ከተማን የመቀየር አቅም እንዳለው በተጨባጭ ያረጋገጠ ደማቅ የታሪክ ምዕራፍ ነው።

 በአዶኒያስ ወልደአረጋይ