Search

የሚኒስትሮች ምክር ቤት የ2019 በጀትን ጨምሮ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳለፈ

ማክሰኞ ሰኔ 02, 2018 146

የሚኒስትሮች ምክር ቤት በዛሬው ዕለት ባካሄደው 56 መደበኛ ስብሰባ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳለፈ፡፡

1. ምክር ቤቱ በቅድሚያ የተወያየው የመካከለኛ ዘመን (2019-2023) የማክሮ ኢኮኖሚና ፊስካል ማዕቀፍ ላይ ነው፡፡

የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርሙ ተግባራዊ ከተደረገ ወዲህ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ካሉበት ተግዳሮቶች እየተላቀቀና የኢኮኖሚው መሰረቶችም እየተጠናከሩ መጥተዋል፡፡

ማዕቀፉ በኢኮኖሚ ሪፎርሙ የተገኙ አበረታች ውጤቶችን ይበልጥ አጠናክሮ ማስቀጠል እንዲያስችልና በዋና ዋና የማክሮ ኢኮኖሚ እና ፊስካል ታሳቢዎች ላይ በመመስረት 2019 በጀት ዓመት የፌዴራል መንግስት በጀት ዝግጅት መነሻ ሆኖ እንዲያገለግል ተዘጋጅቶ ቀርቧል፡፡

ምክር ቤቱም በማዕቀፉ ላይ በሰፊው ከተወያየበት በኋላ በስራ ላይ እንዲውል በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡

2. በመጨረሻም ምክር ቤቱ ውይይቱን ያደረገው 2019 በጀት ዓመት የፌዴራል መንግስት የበጀት ረቂቅ አዋጅ ላይ ነው፡፡

2019 የፌዴራል መንግስት በጀት የአስር አመቱ መሪ የልማት ዕቅድ አካል የሆነው 2019-2021 የልማትና ኢንቨስትመንት ዕቅድ ላይ የተቀመጡ ግቦችንና የመካከለኛ ዘመን (2019-2023) የማክሮ ኢኮኖሚና የፊሲካል ማዕቀፍን መሰረት በማድረግ፣ 2018 በጀት ዓመት የፕሮግራም በጀት አፈጻጸም መነሻ በማድረግ፣ በቀጣይ ሊኖር የሚችለውን የማህበራዊና የኢኮኖሚ ትራንስፎርሜሽን አቅጣጫዎችና አላማዎች እንዲሁም በመንግስት የተቀመጡ ግቦችን ለማሳካት የመንግስትን የፋይናንስ አቅም እና አስፈጻሚ መስሪያ ቤቶች ከተሰጣቸው ተልዕኮና ሃላፊነት አንጻር የሚያስፈልገውን ወጪ በመገምገም ተዘጋጅቶ ቀርቧል፡፡

በዚሁ መሰረትም ለመደበኛ ወጪዎች፣ ለካፒታል ወጪዎች፣ ለክልል መንግስታት ድጋፍ፣ ለዘላቂ የልማት ግቦች ማስፈጸሚያ ድጋፍ የሚውል 2,339,268,126,738 (ሁለት ትሪሊዮን፣ ሶስት መቶ ሰላሳ ዘጠኝ ቢሊዮን፣ ሁለት መቶ ስድሳ ስምንት ሚሊዮን፣ አንድ መቶ ሀያ ስድስት ሺ፣ ሰባት መቶ ሰላሳ ስምንት ብር) በጀት ለምክር ቤቱ ቀርቧል፡፡

ምክር ቤቱም በቀረበው የፌዴራል መንግስት 2019 ረቂቅ በጀት አዋጅ ላይ በሰፊው ከተወያየበት በኋላ ግብአቶችን በማከል ወደ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡