Search

የተቋማት ሪፎርም ለኢትዮጵያ ዘላቂ እና አስተማማኝ ሰላም

ማክሰኞ ሰኔ 02, 2018 101

በኢትዮጵያ የታሪክ እና የፖለቲካ አውድ ውስጥ ሰላም እና ፀጥታ፣ ከጦርነት ወይም ከግጭት መኖር እና አለመኖር ባለፈ ሰፊ መዋቅራዊ ትርጉም አላቸው።

የሀገራችን ዋነኛ የፀጥታ ስጋቶች የሚመነጩት ከድህነት፣ ከዴሞክራሲ እጥረት፣ ከመልካም አስተዳደር መታወክ እና ከማኅበራዊ ፍትህ መጓደል ነው።

ከእነዚህ ውስጣዊ ምክንያቶች በተጨማሪ፣ የኢትዮጵያን ሰላም እና ልማት የማይሹ ታሪካዊ ጠላቶች የውስጥ ተላላኪዎችን በመጠቀም ሰላም ሲነሷት ኖረዋል።

ለዚህም ዓለም ከተፈጠረችበት ጊዜ ጀምሮ የዓባይን ምንጭ ለመቆጣጠር ስታልም የኖረችው ግብጽ ዋነኛዋ ማሳያ ነች።

ግብጾች በተደጋጋሚ ኢትዮጵያን ለመውረር ሙከራ አድርገው ሳይሳካላቸው ሲቀር፣ ኢትዮጵያን እንዳትረጋጋ ማድረግ አማራጭ የሌለው ጉዳይ አድርገው የወሰዱ ከጥንት ጀምሮ ነው።

ይህንን የጥፋት መንገድ የጠቆማቸው የግብጽን ጦር መርቶ ኢትዮጵያን ለመውረር ሞክሮ በጀግኖቹ አፋሮች ድል የተመታው እና እግሩ እንደወጣ የቀረው አማካሪያቸው ሙንዚንገር ነበረ።

ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የኢትዮጵያን የውስጥ ደካማ ጎኖች እና የብሔር ክፍፍሎችን በውክልና ጦርነት መሣሪያነት ሲጠቀሙበት ኖረዋል።

የታላቁ ሕዳሴ ግድብ መገንባት እና ኢትዮጵያ የውኃ ሀብቷን ተጠቅማ ለመልማት የምታደርገውን ጥረትም ወደ ጂኦ-ፖለቲካ ውጥረት በመለወጥ የውስጥ ተላላኪዎችን በመጠቀም የሚችሉትን ሁሉ እያደረጉ ይገኛሉ።

ይህ የሰላም ማጣት ቀውስ ሀገራችንን ከፍተኛ ዋጋ ሲያስከፍል የኖረ ነው። በዓድዋ የሰው ልጆችን ክብር እና ነፃነት ከፍ ያደረገች ሀገር በኢኮኖሚው ረገድ ሉዓላዊነቷን ሙሉ በሙሉ ሳታስከብር እንድትኖር የተገደደችው በዚህ ምክንያት ነው።

ሁሉንም ጉዳይ በጠመንጃ አፈሙዝ የመፍታት አባዜ ደግሞ በሰላማዊ መንገድ ችግሮችን የመፍታት ልማድ እንዳይዳብር እንቅፋት ሆኖ ኖሯል።

ይህንን መዋቅራዊ የሰላም እና የፀጥታ ችግር በዘላቂነት ለመፍታት መንግሥት የተለያዩ ተቋማዊ እርምጃዎችን እየወሰደ ይገኛል። የውይይት ባህሎች ዳብረው ልዩነቶች ሁሉ ወደ ክብ ጠረጴዛ እንዲመጡ በመንግሥት በኩል ያለው ቁርጠኝነት ከፍተኛ ነው።

በተመሳሳይ የፀና ሰላም ለመፍጠር በፀጥታ እና ደኅንነት ተቋማት ላይ ሰፊ መዋቅራዊ ማሻሻያዎች ተደርገዋል።

በአዲሱ የመከላከያ አዋጅ ቁጥር 1286/2015 መሠረት የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ከቀድሞው የርዕዮተ-ዓለም ወገንተኝነት ሙሉ በሙሉ በመላቀቅ ለሀገር እና ለሕዝብ እንዲቆም ተደርጓል።

ሠራዊቱ የሀገር እና የሕዝብ ደጀን እንዲሆን እና ጦርነትን እንዲያርቅ በትጥቅም በአቅምም እንዲዘምን ተደርጓል። ለዚህም የባሕር፣ የሳይበር እና የህዋ መከላከያ ዘርፎችን እንዲያካትት ተደርጓል።

ሌላው የሪፎርሙ አካል የሆነው የፀጥታ እና ደኅንነት ተቋማት ሪፎርም ነው። የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ዘመኑ የደረሰበትን የቴክኖሎጂ እና የሰው ኃይል አቅም በመያዝ፣ ኢትዮጵያን ከክፉዎች ለመጠበቅ ዝግጁነቱን አረጋግጧል።

ለዚህ ዝግጁነቱም 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ወቅት ያሳየው ከፍተኛ ብቃት ተጠቃሽ ነው።

የአዲስ አበባ እና የክልል ፖሊስ ተቋማትም በዚሁ ደረጃ እንዲደራጁ እና ዝግጁ እንዲሆኑ ተደርጓል።

ብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት አገልግሎት እንዲሁም የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አገልግሎት (ኢመደአ) በቅድመ-መከላከል ላይ እየሠሩት ያለው ሥራ ሀገርን ከከፋ ጥፋት እየታደጋት ይገኛል።

እነዚህ ተቋማት የሕዝብ ወገንተኛ በመሆን ከሌሎች የፀጥታ እና ደኅንነት ተቋማት ጋር በቅንጅት በመሥራት ውጤታማ ተግባራትን እያከናወኑ ነው።

በቀጣይም አስተማማኝ ሰላም እና ፀጥታ ሰፍኖ ፊትን ሙሉ በሙሉ ወደ ልማት ለማዞር የሕዝቡ እና የመንግሥት ሚና ወሳኝ ነው።

መንግሥት ሰላም በባሕሪው በኃይል የሚጫን ሳይሆን በዜጎች እምነት እና በፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል ላይ የሚመሠረት መሆኑን በመገንዘብ መሠረታዊ ተቋማዊ ሥራዎችን እየሠራ ነው።

የደኅንነት ተቋማቱ ለሕግ የበላይነት እና ለሕዝብ ደኅንነት ብቻ ተገዢ እንዲሆኑ ሪፎርም የተሠራባቸው ለዚህ ነው።

የተቋማት ግንባታ ሀገረ መንግሥቱን በፀና መሠረት ላይ ለማቆም ዋነኛው አማራጭ መሆኑን በማመንም፣ ተቋማቱን በጥብቅ የሙያ ዲሲፕሊን እየመራቸው ይገኛል።

በለሚ ታደሰ