ኢትዮጵያ በታሪክ በርካታ ፈተናዎችን፣ አለመግባባቶችን፣ የፖለቲካ ሽኩቻዎችን እና ውስጣዊ እና ውጫዊ ፈተናዎችን አልፋ ከዛሬ ደርሳለች።
በታሪኳ ውስጥ የተፈጠሩት ንትርኮች ያተረፉት ነገር ቢኖር ቂም እና ሌላ የግጭት አዙሪትን ብቻ ነበር።
ይሁን እንጂ የዛሬዋ ኢትዮጵያ ችግሮቿን በጠመንጃ ሳይሆን በውይይት፣ በምርጫ እና በተቋማዊ ሂደቶች ለመፍታት የጀመረችው ጉዞ አዎንታዊ ውጤቶች እያስመዘገበ ይገኛል።
ይህ ደግሞ የዴሞክራሲ ባህል እየጠነከረ እና ልዩነቶች እና አለመግባባቶች በሰላማዊ መንገድ የመፍታት አቅም እየሰፋ መምጣቱን ያሳያል።
የዚህ ታሪካዊ ጉዞ አንዱ ትልቅ ምዕራፍ 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በስኬት መጠናቀቅ ነው።
በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎች በሰላም ወጥተው ድምፃቸውን በመስጠት የኢትዮጵያን የዴሞክራሲ ጉዞ ወደ አዲስ ምዕራፍ መሸጋገሩን አረጋግጠዋል።
በዚህም ኢትዮጵያውያን "የሀገራችን ጉዳይ የሚመለከትን እኛን ብቻ ነው፤ የሥልጣን ባለቤቶች እኛ ነን፤ ሥልጣን የሚገኘው ደግሞ ከአፈሙዝ ሳይሆን ከምርጫ ሳጥን ነው" የሚል ግልጽ መልዕክት አስተላልፈዋል።
የዚህ ምርጫ ትልቁ አሸናፊ ሕዝቡ ራሱ ሲሆን በራሱ ፈቃድ በነፃነት እና በዴሞክራሲያዊ መንገድ ፍላጎቱን የገለጸበት፣ የሀገራችንን የወደፊት አቅጣጫ በራሱ ድምፅ የቀረጸበት ታሪካዊ ሂደት መሆኑ ነው።
በሌላ በኩል ኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ሥርዓቷን ለማጽናት የዴሞክራሲ ሂደት ምሰሶ የሆነውን የውይይት መድረክ ከፍታ ወደ ማገባደጃው ደርሳለች።
በመደማመጥ፣ መከባበር እና በጋራ መግባባት ላይ የተመሠረተች ሀገርን ለመገንባት ተስፋ የተጣለበት ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በርካታ ተግባራትን አከናውኖ ለመጨረሻው ምክክር ዝግጅት እያደረገ ነው።
ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ እስካሁን ባከናወነው ሥራ በመላው ኢትዮጵያ የሚገኙ ዜጎች፣ የሃይማኖት መሪዎች፣ የሲቪክ ማኅበራት፣ የወጣቶች እና የሴቶች ተወካዮች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ምሁራን እና የተለያዩ ማኅበረሰቦች አጀንዳቸውን እንዲሰጡ ዕድል ፈጥሯል።
ለዘመናት ሲያከራክሩ የነበሩ ጉዳዮች በአንድ የሀገራዊ መድረክ ላይ ቀርበው እንዲመከሩ መደረጋቸው ኢትዮጵያ በታሪኳ ያገኘችው ትልቅ ስኬት ነው።
የምክክር ኮሚሽኑ አንዱ ትልቅ ስኬት ልዩ ልዩ አስተያየቶችን እና አመለካከቶችን ወደ አንድ ሀገራዊ ሂደት ማምጣቱ ነው።
በማንነት፣ በፌዴራሊዝም፣ በቋንቋ፣ በትርክት፣ በዜግነት እና በሌሎች ወሳኝ ጉዳዮች ዙሪያ ያሉ ሐሳቦች ተሰብስበው ወደ መጨረሻ የምክክር ምዕራፍ እንዲሸጋገሩ መደረጉ የኢትዮጵያን የመደማመጥ ባህል እየተጠናከረ መምጣቱን ያሳያል።
ዛሬ ኢትዮጵያ ከተቃርኖ ወደ ውይይት፣ ከመጠራጠር ወደ መደማመጥ፣ ከመለያየት ወደ መግባባት የምትሸጋገርበት ወሳኝ ምዕራፍ ላይ ትገኛለች።
ምርጫው የሕዝብን ፈቃድ አሳይቷል፤ ምክክሩ ደግሞ ያንን ፈቃድ ወደ ዘላቂ መግባባት እና ወደ ጋራ ራዕይ የሚቀይር ሂደት ነው።
የሀገራዊ ምክክሩ የመጨረሻ ምዕራፍ ሲጠናቀቅ የሚገኙ ውጤቶች ለቀጣይ ትውልድ የሚተላለፉ የመግባቢያ መሠረቶችን ይጥላሉ።
ይህ ሂደት የፖለቲካ መረጋጋትን፣ የማኅበራዊ አንድነትን፣ የኢኮኖሚ ዕድገትን እና የሀገር ግንባታ ጥረቶችን የበለጠ ለማጠናከር ያግዛል።
ኢትዮጵያ መርጣለች፤ በቀጣይ ደግሞ የምክክሯን ፍሬ ታያለች፤ ይህም ከዴሞክራሲ ወደ መግባባት፣ ከመግባባት ወደ ዘላቂ ሰላም የሚወስድ የታሪክ ጉዞ ነው።
በሀብተሚካኤል ክፍሉ