ከንቲባ አዳነች አቤቤ በሦስተኛው ዙር የተጀመሩ እና 13.4 ኪ.ሜ የሚሸፍኑ የኮሪደር ልማት ሥራዎችን አፈፃፀም ዛሬ ማለዳ ገምግመዋል።
የኮሪደሮቹ ልማት በአምስት የኮሪደር መስመሮች ተከፋፍለው እየተሠሩ ሲሆን እነርሱም፦
1- ከቦሌ መድኃኔዓለም እስከ ጎላጎል (የቦሌ አትላስን መንገድ ከመስቀል አደባባ መገናኛ መንገድ ጋር የሚገናኝ)፣
2- ከጎላጎል እስከ እንግሊዝ ኤምባሲ (የቀበና መገናኛ መንገድን ከመስቀል አደባባይ መገናኛ መንገድ ጋር የሚገናኝ)፣
3- ከቦሌ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት በሞኤኮ እስከ ቦሌ መገናኛ መንገድ (የቦሌ አትላስን መንገድ ከቦሌ መገናኛ መንገድ ጋር የሚገናኝ)፣
4- ከኢምፔሪያል በአደይ አበባ ስታዲየም እስከ ሻላ መናፈሻ፣
5- ከውኃ ልማት በአትላስ ያለውን እና ከአትላስ እስከ ቦሌ ሩዋንዳ (የቦሌ አትላስ መንገድን ከመስቀል አደባባይ መገናኛ መንገድ እና ከቦሌ አየር መንገድ ጋር የሚገናኝ)
በከፍተኛ ደረጃ የመንገድ ኔትወርኩን የሚያሰፋ፣ የንግድ ተቋማትን፣ ሰፋፊ የእግረኛ መንገድ፣ የሳይክል መንገድ እና ለትራንስፖርት አገልግሎት ምቹ እንዲሆኑ ተደርገው እየተገነቡም ናቸው።
በተጨማሪም በርካታ የሕዝብ አገልግሎት መስጫ ግንባታዎችን የያዘ እና የግንባታውም ሂደትም በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ከንቲባዋ ገልጸዋል።
በአደይ አበባ ስታዲየም ዙሪያ አስቀድመው የተጀመሩ የኮሪደር እና ሌሎች መሠረተ ልማት ግንባታዎች በፍጥነት እና በጥራት እንዲከናወኑ የማድረግ ሥራ ተጠናክሮ ቀጥሏል።
ከኮሪደሩ በተጨማሪም ለብዙ ዘመናት ተረስቶ የኖረ፣ ከሕዝብ ተወስዶ በግለሰቦች ያለአግባብ ተወሮ ለብዙ ብልሽት ተዳርጎ የኖረውን ቦታ ለሕዝብ አገልግሎት እንዲውል ተደርጎ በመሠራት ላይ ይገኛል።
ፕሮጀክቶቹን እስከ ሰኔ ወር መጨረሻ ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ ለአገልግሎት ለማዋል በትኩረት እየተሠራ መሆኑን ከንቲባ አዳነች በማኅበራዊ ትሥሥር ገጽ ባሰፈሩት መልዕክት ገልጸዋል።