በአፍሪካ ቀንድ የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ መልክዓ ምድር ውስጥ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የጎላ ስፍራ ይዞ የሰነበተ ብሔራዊ አጀንዳ ቢኖር የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ ነው።
ይህ ጥያቄ ለኢትዮጵያውያን የጂኦፖለቲካ ፍላጎት ወይም የትምክህት መግለጫ ሳይሆን ከታሪክ ማኅደር የሚቀዳ ሕጋዊ መብት፣ የ130 ሚሊዮን ሕዝብ የሕልውና ዋስትና እና ለአጠቃላይ የምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና የጋራ ዕድገት የሚበጅ የሰላም ጥሪ ነው።
ታሪክ እንደሚመሰክረው ጥንታዊው የአክሱም ኢምፓየር በዓለም ላይ ከነበሩ አራት ኃያላን መንግሥታት አንዱ ሆኖ እንዲወጣ ያደረገው በቀይ ባሕር ላይ የነበረው የአዱሊስ ወደብ ነው።
አዱሊስ የቅንጦት ዕቃዎች የሚተላለፍበት፣ ከሮም፣ ፋርስ እና ሕንድ የመጡ መርከቦች የሚሰፍሩባት ዓለም አቀፍ የንግድ ማዕከል ነበረች።
ይህ በባሕር ዳርቻ ላይ የነበረው አስተዳደር በመካከለኛው ዘመንም "ምድር ባሕሪ" (የባሕር ምድር) በሚል ስያሜ የኢትዮጵያ ነገሥታት ግብር እየተቀበሉ የመሩት የግብር እና የንግድ ፖሊሲ ያወጡበት ቀጣና ነበር።
በ19ኛው ክፍለ ዘመን የአውሮፓውያን አፍሪካ ቅርጫን ቅርጫ የማድረግ ሽሚያ እና የግብፅ ወረራ በጀመረበት ወቅትም ቢሆን አፄ ዮሐንስ አራተኛ እና ራስ አሉላ አባ ነጋ የግብፅን ጦር በጉንደት እና በጉራዕ ድል በማድረግ የባሕር ዳርቻውን ሉዓላዊነት አስከብረዋል።
እ.ኤ.አ በ1884 በአፄ ዮሐንስ እና እንግሊዞች መካከል የተፈረመው የሄዌት ውል ኢትዮጵያ በምጽዋ በኩል ያላትን የነፃ ዕቃዎች ዝውውር መብት በሕግ ያረጋገጠ ሰነድ ነበር።
የቅኝ ገዥዎች ተንኮል እና የካርታ አወቃቀር ግዛታችንን ቢሸረሽረውም ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ የተመድ ውሳኔ 390 (V) በኢትዮጵያ እና ኤርትራ መካከል የፈጠረው ፌዴሬሽን፣ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ለኢትዮጵያ የባሕር በር ማግኘት ያለውን ወሳኝ መዋቅራዊ ፍላጎት በግልጽ ያፀና ታሪካዊ እውነት ነበር።
የዓለም አቀፍ ሕግ ድንጋጌዎች
የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ ከታሪካዊ ፍትሕ ባሻገር በዘመናዊ ዓለም አቀፍ ሕግጋት ላይ በጥብቅ የተመሠረተ ነው።
ኢትዮጵያ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የባሕር ሕግ ስምምነት (UNCLOS) ፈራሚ ሀገር ናት።
የዚህ ስምምነት አንቀጽ 125 ወደብ አልባ ሀገሮች ወደ ባሕር የመውጣት እና የመግባት፣ በትራንዚት ሀገሮች ግዛት ውስጥም በማንኛውም የትራንስፖርት አማራጭ በነፃነት የመንቀሳቀስ መብት እንዳላቸው በግልጽ ይደነግጋል።
በተጨማሪም አንቀጽ 127 በትራንዚት ሀገሮች በኩል በወደብ አልባ ሀገራት የንግድ ልውውጥ ላይ ያላአግባብ የጉምሩክ ቀረጥ እንዳይጣል ይከለክላል።
ስለዚህ ሀገራችን የምታነሳው ጥያቄ የሌሎችን ሉዓላዊነት የመጋፋት ሳይሆን ዓለም አቀፉ ሕግ ለወደብ አልባ ሀገራት የሰጠውን መብት በዲፕሎማሲያዊ መንገድ የመጠየቅና የመጠቀም ሕጋዊ መብት ነው።
ሁለንተናዊ ጠቀሜታው፡ የኢኮኖሚ መነቃቃት እና ብሔራዊ ደኅንነት
ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት የባሕር በር ባለመኖሩ ምክንያት የምትከፍለው በቢሊየኖች የሚቆጠር የውጭ ምንዛሬ እና የስትራቴጂካዊ ተጋላጭነት ዋጋ እጅግ ከፍተኛ ነው።
ላለፉት ሦስት አሥርት ዓመታት ከ95 በመቶ በላይ የባሕር ንግዷን በአንድ ወደብ (በጅቡቲ) ላይ ብቻ ጥገኛ ማድረጓ ብሔራዊ ደኅንነቷን ለአደጋ ያጋለጠ ነው።
ለጅቡቲ ወደብ በዓመት የሚከፈለው ከ2 ቢሊዮን ዶላር በላይ ክፍያ የሀገራችን ልማት ክፉኛ ይጎዳል።
ይህን የወደብ ክፍያ በየሦስት ዓመቱ አንድ ታላቁ የሕዳሴ ግድብን ሊያስገነባ የሚችል ትልቅ ሀብት እንደማጣት ማለት ነው።
የባሕር በር መኖሩ የሚያስገኛቸው ጥቅሞች
የባሕር በር ማግኘት የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሸጋግር ሁለንተናዊ ፋይዳ አለው።
በኢኮኖሚው ረገድ ለአርሶ አደሩ የሚመጣውን ማዳበሪያ እና ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ መሠረታዊ ሸቀጦችን ዋጋ የሚንረው የወደብ አልባነት ታክስ እንዲቀረፍ በማድረግ የዜጎችን የዕለት ተዕለት የኑሮ ውድነት ጫና በከፍተኛ ደረጃ ያቀልላል።
ይህ የወጪ ቅነሳ በቀጥታ ወደ ውጭ ንግዱ ላይ የሚንጸባረቅ ሲሆን እንደ ቡና፣ የቅባት እህሎች እና የኢንዱስትሪ ውጤቶች ያሉ የሀገራችን ዋነኛ ምርቶች ያለምንም መስተጓጎል እና በዝቅተኛ የትራንስፖርት ወጪ ለዓለም ገበያ ቀርበው ዓለም አቀፋዊ ተወዳዳሪነታቸውን እንዲያረጋግጡ ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል።
ይህ የኢኮኖሚ ጥንካሬ አስተማማኝ ሊሆን የሚችለው ደግሞ ከስትራቴጂካዊ ደኅንነት ጋር ሲቀናጅ ነው።
የባሕር በር ባለቤትነት የኢትዮጵያን የባሕር ኃይል እንደገና በጠንካራ መሠረት ላይ ለማደራጀት በር የሚከፍት ነው።
ይህም የሀገራችን የንግድ መርከቦች ከባሕር ላይ ወንበዴዎች ሥጋት እና በቀይ ባሕር ቀጣና ላይ ከሚታየው ተለዋዋጭ አለመረጋጋት በራስ አቅም ለመጠበቅ ያስችላል።
ይህም ኢትዮጵያ በምሥራቅ አፍሪካ እና በቀይ ባሕር የደኅንነት ጥበቃ ውስጥ ያላትን ወሳኝ እና ተደማጭነት ያለው የፖለቲካ እንዲሁም የዲፕሎማሲ ሚና ከፍ ያደርገዋል።
የጋራ ተጠቃሚነት ዲፕሎማሲ
ዓለም እንደተገነዘበው የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ በሰላም፣ በዲፕሎማሲ እና በጋራ ልማት መርህ ላይ መሰረት ያደረገ ነው።
ሀገራችን የጀመረችው ንቁ ዲፕሎማሲ የጎረቤት ሀገራትን የግዛት አንድነት ሳያናጋ የኢትዮጵያን ሕጋዊና የተረጋገጠ የባሕር በር ፍላጎት ማሟላት እንደሚቻል ያሳየ ዲፕሎማሲያዊ ስኬት ነው።
ኢትዮጵያ የባሕር በር እንዲኖራት የምታደርገው ጥረት የፖለቲካ ፓርቲዎች ወይም የአንድ መሪ አጀንዳ ሳይሆን መላው ሕዝብ በአንድነት ሊቆምለት የሚገባ የትውልድ አደራ እና የብሔራዊ ክብር ጥያቄም ነው።
የኢትዮጵያ ወደ ባሕር መመለስ ጎረቤቶቿን የሚጎዳ ሳይሆን በአፍሪካ ቀንድ አስተማማኝ ሰላም እንዲሰፍን፣ የጋራ ንግድ እንዲያብብ እና ቀጣናው የዓለም አቀፍ ኃይሎች መጫወቻ ከመሆን ይልቅ ራሱን የቻለ ጠንካራ የኢኮኖሚ ማዕከል እንዲሆን የሚያስችል ትልቅ አቅም ነው።
ወደፊትም ቢሆን ይህንን ታሪካዊ እና ሕጋዊ ሥልጣን በሰላማዊ ድርድር እና በቀጣናዊ ትብብር መርህ በማስቀጠል የኢትዮጵያን ትክክለኛ የባሕር ባለድርሻነት ቦታ መልሶ ማረጋገጥ የነገው ብሩህ ተስፋችን ነው።
በበረከት ሽመልስ