በቀደሙት ትውልዶች ጽኑ ትከሻ ላይ ቆሞ፣ የትናንቱን ስብራት በይቅርታና በማስተዋል ጠግኖ፣ የነገዋን የኢትዮጵያ ታላቅነት በክብር ለመቅረጽ የሚታትር አዲስ የህሊና ኃይል በምድራችን ላይ ተነስቷል፤ እርሱም "የመደመር ትውልድ" ነው።
ይህ ትውልድ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የ "መደመር" ፍልስፍና ጥላ ስር የበቀለ፣ የሀገርን ትንሳኤ በዕውቀት፣ በአንድነትና በፈጠራ ከፍታ ላይ ለማቆም የተዘጋጀ ትውልድ ነው።
ፍልስፍናው ከቀደመው የታሪክ ማዕድ መልካሙን የሚወርስ የቃል ኪዳን ወራሽ፣ የጎደለውን የሚሞላ የዕድገት አሻሻይ እንዲሁም ለአዲስ ፈጠራና አድማስ በር የሚከፍት የጥበብ ፈጣሪ አድርጎ ያበጀዋል።
ያለፉትን የታሪክ ስህተቶችና ድክመቶች እያማረሩ ከመኖር ይልቅ፣ በይቅርታና በማስተዋል አርሞ ማሻሻል፣ የቀደሙትን በጎ እሴቶች ማህተም አድርጎ የሚጠብቅ ትውልድ ነው።
በብሔር፣ በሃይማኖትና በየአካባቢው ጠባብ አጥር ሳይታጠር፣ በኢትዮጵያዊነት ታላቅ ጥላ ስር በፍቅርና በስምምነት የሚታቀፍ፣ የአብሮነትን ዜማ የሚዘምር ንቁ ኃይል ነው የመደመር ትዉልድ።
ይህንን የታሪክ አዲስ ምዕራፍ ለመክፈትና ትውልዱን በፅኑ መሰረት ላይ ለመገንባት "የመደመር ትውልድ" የተሰኘው መጽሐፍ መነሻዉ ያደርጓል። መጽሐፉ በወረቀት ላይ የሰፈረ ቀለም ብቻ ሳይሆን አዲሱ ትውልድ በዕውቀት፣ በስነ-ምግባር እና በሀገር ፍቅር ታንጾ እንዲያድግ የተነደፈ የህይወት ካርታ ነው።
ባለፉት የታሪክ ጠባሳዎችና የቁርሾ ሰንሰለቶች ሳይታሰር፣ የዘመኑን የሳይንስና ቴክኖሎጂ ግኝቶች እንዲሁም ዓለም አቀፋዊ እውቀቶችን ታጥቆ ሀገሩን ወደ ብልጽግና ማማ እንዲያወጣ ያነሳሳል።
የሚገርመው ደግሞ፣ የዚህ መጽሐፍ በረከት በንባብና በሃሳብ ብቻ አለመወሰኑ ነው፤ ከሽያጩ የሚገኘው እያንዳንዱ ገቢ በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች ለወጣቶችና ለህፃናት የሚሆኑ የንባብ ማዕከላት፣ ዘመናዊ ቤተ-መጻሕፍት እና የመዝናኛ ስፍራዎችን ለመገንባት በመዋል ላይ ይገኛል።
ይህ ራሱ የመደመር ትልቅና ተግባራዊ ማሳያ ነው፤ ዕውቀት በዕውቀት ላይ እየተደመረ፣ የነገው ትውልድ በነፃነት የሚቀመጥበትንና የሚማርበትን ማዕድ ዛሬውኑ ያዘጋጃል።
የዚህ ትውልድ መለያ መልክአ-ምድሮች በሦስት ታላላቅ ምሶሶዎች ላይ የቆሙ የህይወት መርሆች ናቸው። የመጀመሪያው አዎንታዊ አስተሳሰብ ሲሆን በጥላቻ፣ በወቀሳ፣ በጥርጣሬና በጽልመት ላይ ሳይሆን በብርሃን፣ በተስፋና በመፍትሔ ላይ የሚያተኩር የልብ ስፋትና የበሰለ ስብዕና ነው።
ሁለተኛው የአብሮነት ስሜት ነው፤ በሀገር ውስጥ ያሉትን ልዩነቶች እንደ ጠላትነትና እንደ መራራቂያ ሳይሆን እንደውበትና ጌጥ አይቶ፣ በአንድነትና በወንድማማችነት ገመድ ተሳስሮ ለጋራ ህልም መቆምን፣ አንዱ ለሌላው ጋሻ መሆንን ያስተምራል።
ሦስተኛው ደግሞ ስራ ወዳድነት ነው፤ በፈጠራ፣ በላብ፣ በትጋትና በጠንካራ ስራ የሀገርን ሁለንተናዊ ኢኮኖሚ መለወጥና ከጥገኝነት መላቀቅ እንደሚቻል በተግባር የሚያሳይ ቆራጥነት ነው።
በአጠቃላይ የመደመር ትውልድ ማለት ትናንት በልዩነት የተከፋፈለችና የዛለች ሳይሆን ዛሬና ነገ የበለጸገች፣ የተባበረችና የታፈረች ኢትዮጵያን ለመገንባት ራሱን በዕውቀት፣ በጥበብና በስነ-ምግባር የሚያንጽ አዲስ የወደፊት ተስፋ ነው፤ ይህ የእኛ (የመደመር) ትውልድ የኢትዮጵያን የክብር ትንሳኤ በተግባር የሚያበስር ታላቅ ትዉልድ ነው።