Search

የ5ቱ ዓመታት ገፆች፡ ከግቢ የፈነጠቀው የከተሜነት ብርሃንና የመደመር አሻራ

ረቡዕ ሰኔ 03, 2018 70

ከስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ እስከ ሰባተኛው ምርጫ ዋዜማ የተዘረጉት የ5ቱ ዓመታት ገፆች፣ የኢትዮጵያን የከተሜነትና ክትመት ታሪክ በአዲስ ቀለም የፃፉ ናቸው። በመደመር እይታ፣ ከተሜነት ማለት የህንፃዎች ክምችት ወይንም በምቾት መኖር ብቻ ሳይሆን፤ ከተሞችን አካታች፣ ሥሉጥ (Smart) እና ለኑሮ ምቹ የሆኑ የብልፅግና ማዕከላት ማድረግ ነው።

የመደመር ትውልድ ከተሜነትን የዕውቀት፣ የንግድና የስልጣኔ ኮሪዶር አድርጎ በመሳል፣ የነዋሪውን እለታዊ ኑሮ ከውበት፣ ከአረንጓዴ ልማትና ከዘመናዊነት ጋር በማስተሳሰር ስኬታማ አድርጎታል።

የለውጡ ኃይል ይህን ታላቅ የከተማ ገፅታ ትራንስፎርሜሽን የጀመረው ከሩቅ አልነበረም፤ "ከቢሮ እስከ ሀገር" በሚል ጽኑ እምነት ከራሱ ከሥልጣን ማዕከል፣ ከግቢ ጀመረ። ለዘመናት በምስጢርና በቁልፍ ተዘግቶ፣ አርጅቶና ተረስቶ የነበረው የላይኛው ቤተመንግስት፣ ታሪክንና የተፈጥሮ ውበትን አዋህዶ "አንድነት ፓርክ" ሆኖ ለህዝብ ሲከፈት፣ "በኢትዮጵያ ፈጣንና ጥራት ያለው ፕሮጀክት አይቻልም" የሚለውን የትላንት አስተሳሰብ ከስሩ ሰባበረው። ከግቢ የፈነጠቀው ይህ የውበት፣ የፈጠራና የፍጥነት ብርሃን መላዋን መዲና ለማዳረስ ጊዜ አልወሰደበትም።

በ"ገበታ ለሸገር" ማዕቀፍ የተሰሩት ስራዎች የመደመር ትውልድ የትላንቱን ጠባሳ ያከመባቸው ህያው ምስክሮች ናቸው። እንጨት ለቀማና እርጅና ተጭኖት የተተወው የእንጦጦ ተራራ፣ ማራኪ የተፈጥሮና የመዝናኛ ማዕከል ሆኖ "እንጦጦ ፓርክ"ን ወለደ። የከተማዋን የልብ ትርታ የቀየረው "ወዳጅነት ፓርክ"፣ የቆሻሻ ማራገፊያ የነበሩና መጥፎ ጠረን የሚያውዱ ስፍራዎችን ወደ ውብ አረንጓዴ ስፍራነትና ሰው ሰራሽ ሀይቅነት ቀየራቸው። ትውልድን በዕውቀት ለማነፅ የተገነባው "አብርሆት ቤተ-መጻሕፍት" የከተማችን የብርሃን ማማ ሲሆን፤ የዘመኑን ቴክኖሎጂና ፈጠራ የሚያሳየው "የሳይንስ ሙዚየም" ደግሞ የነገዋን ኢትዮጵያ ከፍታ አመላካች ሆነ።

የዚህ ትውልድ አሻራ በዚህ ብቻ አላበቃም፤ የከተማዋን ታሪካዊ ክብር በሚመጥን መልኩ አዲስ የልማት ማዕበል ተነሳ። ያረጀውና የተጎሳቆለው ታሪካዊው የአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት በዘመናዊ ዲዛይን ታድሶ የከተማዋን ክብር ሲመልስ፤ በፒያሳ እምብርት የጥቁር ህዝቦች የነፃነት ተምሳሌት የሆነው ግዙፉ "የአድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም" ትውልድን ከታሪኩ የሚያስተሳስርና ከተማዋን የሚያስውብ አዲስ የትዕምርት ማማ ሆኖ ተገነባ። 

ከማዘጋጃ ቤት ተነስቶ ፒያሳን አቋርጦ እስከ መስቀል አደባባይ የተዘረጋው ሰፊ የመንገድ ኮሪደር ልማት፤ ለእግረኞችና ለብስክሌት ተጓዦች ምቹ የሆኑ ሰፊ መንገዶችን፣ ውብ መብራቶችንና አረንጓዴ ስፍራዎችን በማካተት የከተማዋን ታሪካዊና ዘመናዊ ክፍሎች በተመስጦ አዋህዷል። ታሪካዊው "መስቀል አደባባይ" ማራኪ ገፅታ ተላብሶ ለትላልቅ ሀገራዊ ኩነቶችና ለህዝብ መዝናኛነት በክብር ሲዘጋጅ፣ ዘመናዊውን "የአንድነት የመኪና ማቆሚያ" ፕሮጀክት በከርሰ-ምድር በማስተናገድ የከተማዋን የትራፊክና የመኪና መጨናነቅ ችግር በዘመናዊና ስልጡን መንገድ ፈትቶታል።

ከስድስተኛው ምርጫ እስከ ሰባተኛው ምርጫ ዋዜማ ያሉት እነዚህ የ5ቱ ዓመታት ገፆች፣ የቃላት ሳይሆን የላብና የተግባር ድርሳናት ናቸው። የመደመር ትውልድ አሮጌውን፣ አፍራሽና የቸልተኝነት የፖለቲካ ባህል ቀብሮ፣ ከተሞችን ዳግም ፈጥሯቸዋል። ይህ ከግቢ የተጀመረውና በአጭር ጊዜ ውስጥ መላዋን መዲና ያዳረሰው የልማት ጅረት፣ ለቀጣዩ ትውልድ የምትመች ኢትዮጵያን ለመገንባት የሚያስችል ጽኑ መሠረት የጣልንባቸው፣ በተግባር የተረጋገጡ የብልፅግና ታሪካዊ ምዕራፎች ናቸው።

የአምስት አመት ቅኝታችን እነሆ ዛሬ ጀምሯል፡፡ አብረን እንዝለቅ!!